የህዳሴው ግድብ ድርድር የዘገየው በግብፅ እና ሱዳን ምክንያት ነው- የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር
የህዳሴው ግድብ ድርድር መቼ ሊጀመር እንደሚችል መረጃ እንደሌለው ሚንስቴሩ አስታውቋል
ኢትዮጵያ ከጥቂት ወራት በኃላ በሴኔጋል ዳካር በሚካሄደው የቻይኛ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ እንደምትሳተፍ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር በሚቀጥልበት ዙሪያ ከሀገራቱ ጋር በመምከር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚንስትሩ በትናንትናው ዕለትም ወደ ሶስቱም ሀገራት በመሄድ ከሀገራቱ ጋር መወያየት የጀመሩ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር በትናንትናው ዕለት በግድቡ ቀጣይ ድርድር ሂደት ዙሪያ መወያየታቸውን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
- ዲ. አር ኮንጎ የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በቶሎ እንዲጀመር እያግባባች ነው
- የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሸ ድርድርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስጀመር እንደሚቻል ዲ.አር ኮንጎ ገለፀች
በዛሬው ዕለትም የዲ.አር.ሲው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከሱዳን እና ግብጽ አቻቸው ጋር በካይሮ እና ካርቱም እንደሚወያዩ ተገልጿል።
የህዳሴ ግድብ ቀጣይ የሶስትዮሽ ድርድር መቼ እንደሚካሄድ እስካሁን እንደማይታወቅ የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ የድርድር ቀኑ ሲታወቅ ኢትዮጵያ ትሳተፋለችም ብለዋል።
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው ካለ ወራትን አስቆጥራል ለምን ድርድሩ ዘገየ? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም ግብጽ እና ሱዳን አቋማቸውን እና ፍላጎታቸውን ስለሚቀያይሩ እንጂ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ ናት ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አምባሳደሩ አክለውም የፊታችን ታህሳስ በዳካር ሴኔጋል ይካሄዳል በሚባለው የአፍሪካ- ቻይና ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ ላይ ከቻይና እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያሳድጉ ውይይቶችን እንደምታካሂድበትም ተገልጿል።
ይሁንና ይህ የባለ ብዙ ወገን ጉባኤ በኮሮና ቫይረስ ስጋት ምክንያት በበይነ መረብ ይካሄድ ወይስ በአካል ይሁን የሚለው እስካሁን አልተወሰነም።