የህዳሴው ግድብ ለስንት አመት ያገለግላል?
ኢትዮጵያ ከ20 አመታት በፊት በአባይ ላይ የምትሰራቸውን ፕሮጀክቶች ዝርዝር ማዘጋጀቷን ተደራዳሪ ዶ/ር ይልማ ገልጸዋል
ግድቡ ለ100 አመታት በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ በዲዛይኑ ላይ ደለል የሚከማችበትን ቦታ አካቷል
ግድቡ ለ100 አመታት በሙሉ አቅሙ ኃይል እንዲያመነጭ በዲዛይኑ ላይ ደለል የሚከማችበትን ቦታ አካቷል
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዲዛይን፣ ግድቡ ለ100 አመታት ያህል የማመንጨት አቅሙ እንዳይቀንስ ደለል የሚያጠራቅምበት ቦታ ተትቶለታል፡፡
በክረምት የሚደፈርሰው የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች የጠራረገውን አፈር ግድቡ ጀርባ ማጠራቀም መጀመሩ የግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት ይፋ ሲደረግ በሚያሳዩ ምስሎች ታይቷል፡፡ ደለሉ በግድቡ በረጅም ጊዜ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር አንድ የግድቡ ተደራዳሪ አብራርተዋል፡፡
ተደራዳሪው ዶ/ር ይልማ ስልሺ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት በግድቡ ዲዛይን ላይ ደለል ለማከማቻ የሚሆን ቦታ ስለተካተተ፣ግድቡ ለ100 አመታት ያህል በሙሉ አቅሙ ማመንጨት ይችላል፡፡
ዶ/ር ይልማ ከ100 አመታ በኋላ የማመንጨት አቅሙ ቀስ እያለ እየቀነሰ እስከ 250 አመታት ያገለግላል ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ ስራን መስራት የደለሉን መጠን መቀንስ እንደሚቻል የገለጹት ዶ/ር ይልማ ነገርግን ወደ ግድቡ የገባውን ደለል ማስወገድ አይቻልም ብለዋል፡፡
“እንኳን እሱን(የህዳሴ ግድቡን) ትንንሾቹን የነቆቃን እንኳን ማስወገድ አይቻልም፡፡ ግን ይሄ አብረህ የምትኖረው ነው፤ አሁን የአሜሪካን ግድቦች ወደ 60 ና 70 አመታት እየሆናቸው ነው፡፡ ከ50እና 60 አመታት በኃላ ቡዙዎቹ ዲኮሚሽንድ/ከአገልግሎት ውጭ ይሆናሉ፡፡ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ፡፡ በአፈር ይሞላሉ፤ የድሮ እርሻ ይጀመራል ማለት ነው፡፡ ቦታው በደለል ስለሚሞላ፡፡ ተመልሶ ወንዙ ይኖራል፤ ፋፏቴ ይኖራል ማለት ነው፡፡”
ዶ/ር ይልማ እንዳብራሩት ከ250 አመት በኃላ የህዳሴ ግድቡ በደለል ከተሞላ ከአገልግሎት ውጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡
በመጀመሪያው አመት የግድቡ ሙሌቱ የዝዋይን ሐይቅ የሚያህል ሐይቅ መፈጠሩን ዶ/ር ይልማ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ይልማ “አሁን ዝዋይን የሚያል ሀይቅ ተፈጥሯል፤ 300 ኪሎሜትር ስኩየር ይሆናል፡፡ ወደፊት ግን የጣናን ግማሽ የሚያክል ሃይቅ ይፈጠራል፡፡ ጣና ክብ ነው፣ይሄ ግን ወንዙን ተከትሎ ወደ 300 ኪሜ ወደ ኋላ ሊደርስ ይችላል፡፡ የት ሊደርስ እንደሚችል ቦታውን አናውቅም ቡሬን ግን አያልፍም፡፡”
ሙሌቱን በተመለከተ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ምን አሉ?
የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብጽና ሱዳን ያለስምምነት ግድቡ እንዳይሞላ ጠንካራ አቋም ይዘው ሲከራከሩ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን አመት ሙሌት አጠናቃለች፤ በዚህ አመት መያዝ የምትፈልገውን 4.9 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር ውሃም መያዟን አስታውቃልች፡፡
ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት ማጠናቀቋን ይፋ ለማድረግ አንድ ሳምንት እስከሚቀር ድረስ ሲያሳስቡ የነበሩት ግብጽና ሱዳን ከሙሌቱ በኋላ ምንም ያሉት ነገር አለመኖሩን ዶ/ር ይልማ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ይልማ “ሙሌቱን ያደረግነው መብታችን ስለሆነ ነው፡፡ በየትኛውም መንገድ የሚከለክለን ስለሌለ ጉልህ ጉዳት ሳናደርስ ሞልተነዋል፡፡ ግብጽና ሱዳን ኮሜንት/አስተያየት አልሰጡም፡፡ በድጋፍም በተቃውሞም ምንም አላሉም፡፡”
ዶ/ር ይልማ ግድቡ ከተሞላ በኃላ “አትሞሉም ቢሉ፤አክሽን/ርምጃ በመውሰድ ለህዝባቸው ማሳየት ስላለባቸው አጣብቂኝ ውስጥ ስለሚገቡ ነው” ምንም አስተያየት ያልሰጡት ብለዋል፡፡
ክረምት ለመሙላት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ግድቡ መሞላቱን ገልጸዋል፡፡
በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል “ከፍተኛ ልዩነት ነው ያለን”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የግድቡ የመጀመሪያ አመት ሙሌት መጠናቀቁን ይፋ ባደረጉት መግለጫ በአፍካ ህብረት በሚመራው ድርድር ሶስቱ ሀገራት “የጋራ መግባባት” ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
አሁን ላይ ጉዳዩ በመሪዎች ደረጃ እንደተያዘ የገለጹት ዶ/ር ይልማ አሁንም በተለይ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ይናገራሉ፡፡ በግድቡ ዙሪያ ሁሉም የራሱን ፍላጎት እየጻፈ ነው ያሉት ዶ/ር ይልማ “ሱዳን መሃል ፖዚሽን በመያዝ 95 በመቶ በቴክኒካል ጉዳዮች ስምምነት አለ ይላሉ” ብለዋል፡፡
ዶ/ር “ሱዳንኖች መሃል ፖዚሽን ይወስዱና አስታራቂ ነን ይላሉ፡፡ ፖዘቲቭ/መልካም እናውራ ይላሉ፡፡ እንደዛአይነት ቁጥር የለም፡፡ ሲሞላ ምናልባት 85 ሊደርስ ይችላል፡፡ከተሞላ በኃላ ይሄ አይደለም፡፡ “
ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የምትሰራቸው ፕሮጀክቶች ዝርዝር አለ
ዶ/ር ይልማ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከግድቡ በተጨማሪ በአባይ ወንዝ ላይ ልትስራ የምትችላቸውን ፕሮጀክቶች ዝርዝር ከ20 አመታት በፊት አዘጋጅታለች ብለዋል፡፡
“የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ድርጅት አለ፡፡ ግብጾችም ሱዳችም ያሉበት…የኛ ፕሮጀክቶች ዝርዝር ከኤ እስከ ዜድ/ በጠቅላላ ሱዳኖችም ግብጾችም ያውቁታል፡፡ ያ ዶክመንት እዛም(በግብጽና በሱዳን) አለ፡፡ ያውቁታል፡፡”
በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች በእቅዳቸው መሰረት ይሰራሉ ያሉት ዶ/ር ይልማ “የትኛውን ፕሮጅክት መቼ ላስገባው የሚለው“ ጊዜው ሲደርስ ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ፤ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ግድብ እሰጣገባ ውስጥ ገብተው ቆይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ የውሃ ድርሻ ተጠቅማ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ ሳታሳድር ለልማት አለማ ግድብ መገንባቷ ተገቢ መሆኑን በተደጋጋሚ ስገልጽ ቆይታለች፡፡ ሱዳን የግድቡን መገንባት ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደማትቃወም ገልጻ፤ነገርግን አስተዳደሩና አሞላሉን በሚመለከት የሶስትዮች ስምምነት መኖር አለበት የሚል አቋም ስታንጸባርቅ ቆይታለች፡፡
ግብጽ በአንጻሩ በ1950ዎቹ በቅኝ ግዛት ወቅት የተፈረሙ ስምምነቶችን ጭምር በመጥቀስ ታሪካዊ የውሃ ድርሻየ ይቀንሳል የሚል አቤታቱ እያሰማች ነው፤የግድቡን መገንባትም ትቃወም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ግን ይህ ስምምንት እንደማይመለከታት ገልጻለች፡፡
በየካቲት ወር በዋሸንግተን ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በኢትዮጵያ ተቃውሞ ከተቋረጠ በኋላ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲመራ ስምምነት ላይ ደርሰው፤ ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡