የመንግስት ሰራተኞች የስራ ሰዓት ሽግሽግም ተደርጓል
ኮድ 2 ተሽከርካሪዎች በፈረቃ ሊንቀሳቀሱ ነው
ከአሁን በኋላ በአዲስ አበባ ኮድ-2 የሆኑ የግል ወይም የቤት ተሽከርካሪዎች በሰሌዳ ቁጥር ሙሉና ጎዶሎነት በፈረቃ ይንቀሳቀሳሉ ተብሏል፡፡
ይህ የተባለው የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ኮሚቴ በወጣው የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃጸም መመሪያ መሰረት ነው፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መሰረት የሰሌዳ ቁጥራቸው መጨረሻ ጎዶሎ የሆነ ተሽከርካሪዎች መንቀሳቀስ የሚችሉት ሰኞ፣ ረቡዕ እና አርብ ሲሆን ፥ የሰሌዳቸው የመጨረሻ ቁጥር ሙሉ ወይም ዜሮ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ደግሞ መንቀሳቀስ የሚችሉት ማክሰኞ፣ ሀሙስ እና ቅዳሜ ይንቀሳቀሳሉ፡፡
እሁድ እለት ደግሞ ሁሉም ተሸከርካሪዎች መንቀሳቀስ ተፈቅዶላቸዋል።
መመሪያው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተንተርሶ የወጣ ነው፡፡ በክልሎች እንደየተጨባጭ ሁኔታቸው መመሪያቸውን አውጥተው እንደሚተገብሩትም ተገልጿል
የመንግስት ሰራተኞች የስራ ሰዓት ሽግሽግ
በፌዴራልና በአዲስ አበባ በመንግስት ሰራተኞች የስራ ሰዓት ላይ ሽግሽግ ተደርጓል፡፡
ሽግሽጉ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፤ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለዉን ጉዳት ለመቀነስ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማስፈፀም በሚኒስትሮች ኮሚቴ በወጣው የትራንስፖርት ዘርፍ አፈፃጸም መመሪያ መሰረት የተደረገ ነው፡፡
በመመሪያው መሰረትም የፌዴራል ሠራተኞች ሥራ የመግቢያ ከጠዋቱ 1 ሰዓት 30 ሲሆን ከስራ መውጫ ሰዓት ደግሞ ከቀኑ 9፡30 ይሆናል፡፡ ይህ የሥራ ሰዓት ሽግሽግ ሠራተኞቹ በስራ ሰዓት መካከል የሚያገኙትን የእረፍት ጊዜ እንደማያሳጣቸው መመሪያውን በማስመልከት መግለጫን የሰጡት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች ደግሞ ረፋድ 3 ሰዓት ከ30 ገብተው 11 ሰዓት ከ30 እንደሚወጡ አል አይን አማርኛ ከባለስልጣኑ ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ክልሎች እንደየተጨባጭ ሁኔታቸው የራሳቸውን የስራ ሰዓት መመሪያ እንደሚያወጡም መረጃው ጠቁሟል፡፡
መናኸሪያዎች በተጓዦች ከመጨናነቅም በላይ አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ አይደለም
ሃገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎትን በሚሰጡ እና አዲስ አበባ በሚገኙ መናኸሪያዎች የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሚል ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተጣጥሞ የወጣው መመሪያ በወጉ እየተገበረ እንዳይደለ አል ዐይን አማርኛ ከተለያዩ ምንጮች ያገኛቸው መረጃዎች አልክተዋል፡፡
የፋሲካ በዓልን ታሳቢ አድርገው ወደ ቤተሰቦቻቸው ለመሄድ በመነኸሪያዎች የተሰባሰቡ ተጓዦችን የያዙ ምስሎችም በየማህበራዊ ሚዲያው ሲሽከረከሩ ውለዋል፡፡
ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ይግዛው ዳኘው መናኸሪያዎች የመጨናነቃቸውን እውነታነት አስረግጠውልናል፡፡
በየትኛውም ቦታ የሚገኙ መናኸሪያዎች ከመደበኛው የዕለት የስምሪት መጠን 50% ቀንሰው ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ እንዲችሉ መመሪያ ቢወጣም ከመናኸሪያዎቹ ተዘግቶ መክረምና ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ መጨናነቅ መፈጠሩን ገልጸውልናል፡፡
በየመነኸሪያውና በየተሽከርካሪው አስፈላጊ እና አስገዳኝ የተባሉ ጥንቃቄዎች በሚጠበቀው ልክ እየተተገበሩ እንዳልሆነም ዳይሬክተሩ አልሸሸጉም፡፡
ቀደም ባሉት ቀናት ተስተውለው የነበሩት የጥንቃቄ መንገዶቹን የመከተል ዓይነት አዝማሚያዎች አሁን ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ እየተተገበሩ እንዳይደለም ገልጸዋል፡፡
በተፈጠረው ከፍተኛ መጨናነቅና ጥግግት ምክንያት ውሃና ሳሙናን መሰል የንጽህና ቁሳቁሶችን ማቅረብ ተሽርካሪዎችንም ጸረ ተህዋሲ ኬሚካሎችን መርጨት እንዳልተቻለም ነው አቶ ይግዛው የተናገሩት፡፡
ሆኖም ይህ ሁኔታ አይቀጥልም እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡ የወጣው መመሪያም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በከተማዋ መውጫ ባሉ 6 መናኸሪያዎች እና በሌሎችም ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡