ኢትዮጵያ “ኮቪድ-19 ድንገተኛ የህብረተሰብ ጤና ስጋትነቱ ቢያበቃም የመከላከል ጥረቴ አይቆምም” አለች
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 በጠና ከተማሙት 6 በመቶዎች ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የጤና እክል አጋጥሟቸዋል ተባለ
7 ሽህ 600 የሚሆኑ ሰዎች በወረርሽኙ ህይወታቸው ማለፉን ጤና ሚንስቴር አስታውቋል
ጤና ሚንስቴር መጋቢት 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያ የገባው ኮቪድ-19 ድንገተኛ የህብረተሰብ የጤና ስጋትነቱ ቢያበቃም አዲስ ዝርያ ሊመጣ ስለሚችል የመከላከል ጥረቴ አያበቃም ብሏል።
የዓለም የጤና ድርጅት ከሦስት ዓመታት በኋላ ኮቪድ-19 የዓለም የጤና አደጋነቱ ማብቃቱን ባለፈው ሳምንት አውጇል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ ሀገራት ቫይረሱን ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ጋር መቆጣጠር ይችላሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር ወረርሽኙን አስመልክቶ ባስወጣው መግለጫ፤ አዲስ ዝርያ ሊመጣ ስለሚችል የመከላከል ጥረቴ አያበቃም ብሏል።
ሚሊዮኖች አሁንም በሳርስ ኮቭ-2 እና በአዲስ የቫይረሱ ዝርያ ሊያዙ ስለሚችሉ አሳሳቢነቱ እንዳላበቃ ገልጿል።
ሚንስቴሩ ወረርሽኙ ከገባበት 2012 እስከ ሚያዚያ 27፤ 2015 ዓ.ም. ድረስ ስርጭቱን ለመግታትና ለመቆጣጠር የተለያዩ ስራዎችን መሰራቱን ተናግሯል።
በሀገሪቱ ከአምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የላብራቶሪ ምርመራዎች ተደርገው፤ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።
7 ሽህ 600 የሚሆኑ ሰዎችም በወረርሽኙ ህይወታቸው ማለፉን ጤና ሚንስቴር አስታውቋል።
በጽኑ ታመው አገግመዋል ከተባሉ ሰዎች መካከል 6 በመቶ ያህሉ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ የጤና እክል አጋጥሟቸዋል ተብሏል።
44 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ጊዜ፣ 37 ነጥብ ሰባት ሚሊዮኖቹ ደግሞ ሁለት ጊዜ መከተባቸውን ያሳወቀው ጤና ሚንስቴር፤ በሀገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል ብሏል።
ሆኖም ያለው ጤና ሚንስቴር አዲስ የወረርሽኙ ዝርያ ሊከሰት ስለሚችል የመከላከል ጥረቱ ይቀጥላል በማለት አክሏል፡፡
ሁሉም ዜጎች በጤና ተቋማት በነጻ የሚሰጠውን ክትባት እንዲወስዱም አሳስቧል።