በዓለም ላይ በየአራት ሰከንድ አንድ ሰው በረሃብ እንደሚሞት ተገለፀ
ከ200 የሚበልጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እየከፋ የመጣውን የረሃብ አደጋ አስመልክቶ ለዓለም መሪዎች ደብዳቤ ጽፈዋል
ድርጅቶቹ በየቀኑ እስከ 19,700 የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ ይሞታሉ ተብሎ እንደሚገመት አስታውቀዋል
በዓለማችን ላይ በየአራት ሰከንድ አንድ ሰው በረሃብ እንደሚሞት የተለያዩ መንግሰታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አስታወቁ።
ከ200 በላይ ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “እየተባባሰ ያለውን ዓለም አቀፍ የረሃብ ቀውስ ለማስቆም” ወሳኝ ዓለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።
ከ75 ሀገራት የተውጣጡት 230 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኒውዮርክ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለተሳተፉ የዓለም ሀገራት መሪዎች ግልጽ ድብዳቤ ጽፈዋል።
ለዓለም መሪዎች ግልጽ ድብዳቤ ከጻፉ መካከልም ኦክስፋም፣ ሴቭ ዘ ቺልድረን እና ፕላን ኢንተርናሽናል የሚገኙበት ሲሆን፤ በዓለም ላይ ያለው የረሃብ አደጋ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ ቁጣቸውን ገልፀዋል።
መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው “በአሁኑ ጊዜ 345 ሚሊዮን የዓለማችን ህዝቦች አጣዳፊ ረሃብ እየተሰቃዩ ነው ያሉ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከ 2019 ጀምሮ በእጥፍ ጨምሯል” ብለዋል።
በየቀኑ እስከ 19,700 የሚደርሱ ሰዎች በረሃብ ይሞታሉ ተብሎ እንደሚገመት የገለጹት ድርጅቶቹ ይህ ሲከፋፈልም በየአራት ሰከንድ አንድ ሰው በረሃብ እንደሚሞት እንደሚያመላክት አስታውቀዋል።
በዓለም ዙሪያ 45 ሀገሮች ውስጥ የሚገኙ 50 ሚሊዮን ሰዎች የረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ ናቸው ሲሉም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቹ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
የዓለም ሀገራት መሪዎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን ረሃብን ዳግም እንደማይፈቅዱ ቃል ቢገቡም፣ አሁንም በሶማሊያ ረሃብ መፈጠሩን ነው ድርጅቶቹ ያስታወቁት።
በረሃብ አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ለመታደግ እንዲሁም የራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን የምግብ ፍላጎት እንዲያሟሉ አፋጣኝ ፋጣኝ የህይወት አድን ምግብ እና የረጅም ጊዜ ድጋፍ ላይ ለማተኮር ለአፍታ መጠበቅ የለብንም ሲሉም አሳስበዋል።