ዓለም አቀፍ ጥናቱ የኢትዮጵያን የመደራደር አቅም ያሳድገዋል ተብሏል
በኢትዮጵያ በኦጋዴን አካባቢ 7 ትሪሊዮን ኪዪቢክ ጫማ (200 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ገደማ) የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት መኖሩ የሚያረጋግጥ ጥናት ይፋ ተደረገ።
የማዕድን ሚንስቴር ከአሜሪካው ኔዘርላንድ ስዌል ኤንድ አሶሲሼየትስ ኢንክ ኩባንያ (ኤልሲኤአይ) የጥናት ተቋም ጋር በመተባበር ያስጠናውን የነዳጅ ክምችት ጥናት ይፋ አድርጓል።
በዚህ መርሀ ግብር ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ በኦጋዴን ተፋሰስ 7 ትሪሊየን ጫማ ጥልቀት ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት እንዳላት በጥናቱ ተረጋግጧል ተብሏል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ ( ኢ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት ጥናቱ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን የመደራደር አቅም ያሳድገዋል ብለዋል።
“ከዚህ ቀደም የነበሩ ኩባንዎች ምን ያህል ክምችት እንዳለን አይነግሩንም ነበር” ያሉት ሚኒስትሩ አሁን የተጠናው ጥናት ግን ለክምችቱ መጠን ዓለም አቀፍ ማረጋገጫ መስጠቱን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የነዳጅ ሀብት መጠናችን በዚህ ጥናት መረጋገጡ በተስፋ ብቻ ሲነገረን የነበረው ነገር ወደ እውነትነት እንዲቀየር ያደርጋልም ሲሉ ሚንስትሩ አክለዋል።
ይህ የነዳጅ ሀብት የአዋጭነት ጥናት ለአራት ወራት የተካሄደ ሲሆን ጥናቱ ኢትዮጵያ በተለምዶ ከሚባለው በትክክል ያላት የተፈጥሮ ነዳጅ መጠን ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነም በጥናቱ ርክክብ ወቅት ተገልጿል።
የጥናቱን ውጤት ይፋ በማድረጉ እና የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተሉያዩ ተቋማት ሚኒስትሮችን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካዮችም ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ በ2010 ሰኔ ወር ላይ በቀን እስከ 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማምረት ሙከራ ጀምራ አንደነበረ መገለጹ ይታወሳል።
ሆኖም ግን በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ላይ በኦጋዴን አካባቢ በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ የነበረው ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣት ስራው መቆሙን የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር ገልጾ ነበር።