በወጋገን ባንክ 1 ዶላር በ77 ብር እየተገዛ በ79 እየተሸጠ ይገኛል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በዲሱን የምንዛሬ ተመን ከሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል ወደሚወስንበት የገበያ ሥርዓት መሸጋገሩን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊነትን ተከትሎ በምንዛሬ ተመን በአንድ ዶላር ላይ በአማካይ እስከ 20 ብር ጭማሪ ታይቷል።
ይህንን ተከትሎ ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ ከሳንቲሞች እስከ 3 ብር የሚደርስ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ባወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን መሰረት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ77.1280 ብር እየተገዛ በ78.6706 ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ዩሮ 83.3754 ብር እየተገዛ በ85.0429 ብር እየተሸጠ መዋሉን የባንኩ የዋጋ ዝርዝር አስታውቋል።
በአዋሽ ባንክ በዛሬው እለት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ77.1942 ብር እየተገዛ በ78.7381ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
አንድ ዩሮ ደግሞ 83.7018 ብር እየተገዛ በ85.3759ብር እየተሸጠ መዋሉን የባንኩ የዋጋ ዝርዝር አስታውቋል።
በወጋገን ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ77.7401 ብር እየተገዛ በ79.2949 ብር እየተሸጠ መሆኑን ባንኩ ያወጣው የዋጋ ዝረዝር ያመለክታል።
በዘመን ባንክ ደግሞ በዛሬው እለት አንድ የአሜሪካ ዶላር በ76.2391 ብር እየተገዛ በ77.7639ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ባንክ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ዝር ዝር ስንመለከተም አንድ የአሜሪካ ዶላር በ74.7382 ብር እየተገዛ በ76.2329 ብር እየተሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
በሌሎች ባኮችም የውጨ ምንዛሬ መግዣ እና መሸጫ ላይ የሳንቲም ልዩነቶች መታየታቸውን መታዘብ ችለናል።