የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለ1 ሳምንት እንዲዘጉ ተወሰነ
ትምህርት ቤቶቹ ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2014ዓ.ም እንደሚዘጉ የትምህር ሚኒስቴር አስታውቋል
ትምህርት ቤቶቹ ሲዘጉም ያልተሰበሰቡ የዘማች ሰብል የመሰብሰብ ዘመቻዎች በስፋት እንደሚካሄዱ አስታውቋል
ሁሉም የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለአንድ ሳምንት ዝግ እንዲሆኑ ውሳሄ መተላፉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ውሳኔው የተላለፈው የትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮ ከክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የትምህርት ቢሮ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት የጋራ ውይይት ነው።
በዚህም ትምህርት ቤቶቹ ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2014ዓ.ም እንደሚዘጉና ተማሪዎች፣ መምህራን እና ሰራተኞች ለዚህ ሃገራዊ ትግል እነደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ተወስኗል።
ትምህርት ቤቶቹ ዝግ በሚሆኑበት ወቅትም ያልተሰበሰቡ የዘማች ሰብል መሰብሰብና ቤተሰብን የመርዳት ዘመቻዎች በስፋት እደሚካሄዱም የትምህርት ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
በዚህ ሂደት ትምህርት የቆመባቸው ቀናቶች በሙሉ ትምህር ቤቶች በሚያወጡት የማካካሻ መርሃግብር መሰረት እንዲካካስ እንደሚደረግም ተገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በበሰጡት መግለጫ፤ “ሀገር ከሌለች መኖር ስለማይቻል ሁሉም ሀገሩን የመጠበቅ ሃላፊነት አለበት፤ ስለዚህም የትምህርት ሴክተሩ ያለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት ይወጣል” ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር በትምህርት ዘርፉ ውስጥ ያሉ አካላት ገንዘብ በማዋጣት፣ ደም በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀት እንዲሳተፉም ውሳኔ ተላልፏል።
ተማሪዎችም በዚህ ወቅት ሀገራዊ ግዴታቸውን በመወጣት ሀገሪቱን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።