ፎርብስ ኢትዮጵያን እንዴት መረጠ?
ለዚህም እጅግ አስደናቂ ያላቸውን የሃገሪቱን ታሪካዊ ስረመሰረቶች፣ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ሃብቶች በምክንያትነት አስቀምጧል
መጽሄቱ ከኮሮና ወረርሽኝ ማግስት አብዝተው ሊጎበኙ ከሚችሉ ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች ብሏል
ኢትዮጵያ ከኮሮና ወረርሽኝ ማግስት አብዝተው ሊጎበኙ ከሚችሉ ሃገራት ዝርዝር ውስጥ ተካተተች
ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከኮሮና ወረርሽኝ ማግስት አብዝተው ሊጎበኙ ከሚችሉ ሃገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች ብሏል፡፡
መጽሄቱ በህይወት ቅጥ (ላይፍ ስታይል) አምዱ ከወረርሽኙ ማግስት በቱሪስቶች የመዘውተር እና በማዕከልነት የመጠቀስ እምቅ አቅም ያላቸውን ሰባት የዓለም ሃገራት ዝርዝር አስቀምጧል፡፡
ሃገራቱ በዘርፉ በቀዳሚነት ለመጠቀስ የሚያስችል አቅም ቢኖራቸውም ዝቅ ያለ ግምት ተሰጥቷቸው እንደቆየም ነው የሚጠቅሰው፡፡
ወረርሽኙ የቱሪዝም ዘርፉን ክፉኛ እየፈተነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ፈተናውን ለመሻገር የሚያስችል ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል ያለም ሲሆን አጋጣሚውን እንደ መልካም እድል ሊጠቀሙት እንደሚችሉ እና ይህን ለማድረግ የሚስችል ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ እንዲሁም ታሪካዊ ሃብቶች እንዳሏቸውም ይዘረዝራል፡፡
ከነዚህ ሃገራት መካከልም ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡
አፍሪካን አፍሪካ ካደረጉ 54 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያ እጅግ አስደናቂ ታሪካዊ ስረመሰረት እንዳላት ለመከራከር ይቻላል የሚለው መጽሄቱ ክርስትናን ለመቀበል ከቻሉ የምድራችን ስልጣኔዎች ሁለተኛው የኢትዮጵያ እንደነበረ፣ የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎችን በጦርነት አንገት ያስደፋች ብቸኛዋ አፍሪካዊ ሃገር እንደሆነች እና ምድረ ቀደምትነቷን ለዚህ ከብዙ በጥቂቱ ማሳያዎች ናቸው ይላል፡፡
ቱሪስቶች ወደዚህች ታሪካዊ ሃገር ጎራ ቢሉ ከታሪካዊ እሴቶቿ በተጨማሪ ከዓይነተ ብዙ ተፈጥሯዊ ሃብቶቿ ብዙ ሊያተርፉ እንደሚችሉ፤ ይህ ባይሆን እንኳን ከተወዳጁ የኢትዮጵያውያን የእለት ምግብ ’እንጀራ‘ን ጨምሮ ከባህላዊ የሃገሪቱ ምግቦች ሊቋደሱ እንደሚችሉም ይዘረዝራል ፎርብስ፡፡
(ከጥቂት አመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ታዋቂው የሆሊውድ አክተር ጃኪ ቻን)
ኢራን፣ሚያንማር (በርማ)፣ጆርጂያ፣ፊሊፒንስ፣ስሎቬንያ እና ቱኒዚያ ኢትዮጵያን ተከትለው በመጽሄቱ የተጠቀሱ ሃገራት ናቸው፡፡