“በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን”- ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ
“የሶማሊያ ገዢዎችች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራታቸው አሳፋሪ ተግባር ነው” ብለዋል
“በተሳሳተ ስሌት ትንኮሳ ለመፈፀም ከተሞከረ ሀገራችንን ለመከላከል ሁሌም ዝግጁ መሆናችንን ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል
የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ “በኢትዮጵያ ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን” አሉ።
በምስራቅ ዕዝ 47ኛ የምስረታ ክብረ በዓል በተለያዩ ስነ ስርዓቶች ሲከበር የቆየ ሲሆን፤ በዘሬው እለትም በሀርረ ከተማ የማጠቃለያ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
በምስራቅ እዝ የምስረታ በዓል ላይ የተገኙት የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ፤ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ከቅጥረኛና አኩራፊ ሀይሎች ጋር በመተባበር ከዕድገታችን ለማስቀረት እየሞከሩ ነው ብለዋል።
ሆኖም ግን የኢትዮፕያ ሠራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ለማስቀጠል በተሟላ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
“የኢትዮጵያ ሠራዊት ደግፎ ያቋቋማቸውና ህዝቡን የማይወክሉ አንዳንድ የሶማሊያ ገዢ መደቦች ከታሪካዊ ጠላቶቻችንና ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመቀናጀት በሀገራችንና በሰራዊቱ ላይ ስም የማጥፋት ዘመቻ ላይ መሰማራታቸው አሳፋሪ ተግባር ነው” ብለዋል።
“የሶማሊያ ገዥዎች የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ዓላማ ለማስፈፀም እያደረጉት ያለውን ያልተገባ እንቅስቃሴ በሶማሊያ ህዝብ ዘንድ በግልፅ ተቃውሞ ገጥሞታል” ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ።
ሆኖም ግን “በተሳሳተ ስሌት ትንኮሳ ለመፈፀም ከተሞከረ ለምንወዳትና ሳንሰሰት ህይወታችንን ለምንሰጣት ሀገራችንን ለመከላከል ሁሌም ዝግጁ መሆናችንን ሊታወቅ ይገባል” ማለታቸውንም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
“የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከታሪካዊ ጠላቶች ተልዕኮ ተቀብለው ሀገር የወረሩና በሽብር ለመሰማራት የሞከሩ ሀይሎችን ያሉበት ቦታ በመግባት ሲያጠፋ ቆይቷል” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ፤ “በሀገሪቱ ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ትንኮሳ ለመከላከል በተሟላ ዝግጁነት ላይ እንገኛለን” ብለዋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ባሳለፍነው ሐሙስ በጅግጅጋ በተካሄደ የምስራቅ እዝ የምስረታ በዓል ላይ “ሠራዊታችን ሀገራችንን ለመውረር የሞከሩ ሀይሎች ለመመከት የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛል” ማለታቸው ይታወሳል።
ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም ሀገርን ከጥቃት ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ከሞከሩ ዳግመኛ እንዳያስቡት አድርጎ ለመመከት የሚያስችል ዝግጁነት መኖሩንም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት እንዲሁም ግብጽ ሁለት ወታደራዊ እቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን መሳርያዎችን አሸክማ ወደ ሞቃዲሾ መላኳን ተከትሎ በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል።
ሶማሊያ ከግብጽ ጋር ወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ካይሮ ሁለት ወታደራዊ እቃ ጫኝ አውሮፕላኖችን መሳርያዎችን አሸክማ ወደ ሞቃዲሾ ልካለች።
ከዚህ ባለፈም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን በሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ለማሰማራት ግብጽ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።
ይህንን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል ሲል የከሰሰው የኢትዮጵያ መንግስት ኢትዮጵያ ሁኔታውን አጇን አጣጥፋ እንደማትመለከት አቋሙን ገልጿል።
በነዚህ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሰሞኑ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከፍ ያለ ውዝግብ እና ውጥረት ውስጥ ይገኛል።