የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር በምስል
በዓሉ በተለይም በመስቀል አደባባይ ሲከበር የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪ ወጣቶች ዝማሬዎችን አቅርበዋል
የደመራ በዓል ከ11 አመት በፊት በዩኔስኮ የአለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል
የመስቀል ደመራ በዓል በዛሬው እለት ተከብሮ ውሏል።
በዓሉ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በመስቀል አደባባይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤት ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ደመራውን ባርከው ባስተላለፉት መልዕክት፥ መስቀል ከቁሳዊ ይልቅ መንፈሳዊ ሀይል እንደሚበልጥ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮችን መስቀሉ ባስተማረው መሰረት በሰላም በእኩልነትና በፍቅር መፍታት እንደሚገባ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
የደመራ በዓል መስቀሉን ለማግኘት ንግስት ኢሌኒ ፍላጋ ያስጀመሩበት ሰለሆነ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ሀይማኖታዊ በዓል ነው።
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪም በማህበረሰባዊ በዓልነቱ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችም በተለያዩ መልኩ እያከበሩት ይገኛሉ።
የደመራ በዓል በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችም የተከበረ ሲሆን፥ ምእመናን ከየአጥቢያ ቤተክርስቲያናት ሲመለሱም በቤታቸው ደመራ በመለኮስ ያከብሩታል።
የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ባሉት ባህላዊ ትእይንቶቹ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወሳል።