የመስቀል ደመራ በዓል ተከበረ
የመስቀል በዓል በዓለም ቅርስነት ከ10 ዓመት በፊት በዩኔስኮ መመዝገቡ ይታወሳል
በዓሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በአደባባዮች ላይ መከበሩ ተገልጿል
የመስቀል ደመራ በዓል ተከበረ።
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ ደማቅ በዓል ከሆኑ ሀይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሆነው የመስቀል ደመራ በዓል ተከብሯል።
በዓሉ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 ምሽት ላይ በአደባባዮች ላይ ይከበራል።
ይህ በዓል ከሀይማኖቱ አማኞች በዘለለ በውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ተወዳጅ በዓል ሲሆን የ2016 በዓልም የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው የሀገሪቱ ቦታዎች የተከበረው ይህ በዓል የሀይማኖቱ ተከታዮች የተለያዩ ሀይማኖታዊ ዝግጅቶችን አቅርበዋል።
በአዲስ አበባም በመስቀል አደባባይ የእምነቱ ተከታዮች፣ የሀይማኖት መምህራን፣ የሀገር እና ከተማ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ጎብኚዎች ፣የጸጥታ ሰራተኞች እና ሎሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።
የቤተክርስቲያኗ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅና የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አብርሃም በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር መስቀል በፈጣሪና በሰው ልጆች እርቅ የተፈጠረበት፤ ጥላቻና መከፋፈል የተሸነፈበት ነው ብለዋል።
"መስቀል የተለያዩትን የሚያሰባስብ እና የተጣሉትን የሚያስታርቅ የሰላምና የእርቅ ተምሳሌት ነው" ያሉት አቡነ አብርሀም ምዕመናን የመስቀሉን አስተምህሮ እንዲከተሉም በንግግራቸው ላይ ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ ጥበብ ቢሮ ሀላፊ ሒሩት ካሰው በበኩላቸው በዓሉ መዋደድን እና አንድነታችንን የምናሳይበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
የመስቀል በዓል ከ10 ዓመት በፊት በዓለም የቅርስ፣ ባህልና ትምህርት ወይም ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ሆኗልም ብለዋል።
በዓሉ በአዲስ አበባ ከመስቀል አደባባይ በተጨማሪም በከተማዋ ባሉ የመኖሪያ መንደሮች ውስጥ ባሉ ስፍራዎችም ተከብሯል።
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪም በማህበረሰባዊ በዓልነቱ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችም በተለያዩ መልኩ እያከበሩት ይገኛሉ።