የመስቀል በዓል ከኃይማኖት እና ባህል አንጻር በኢትዮጵያ
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ በዛሬው እለት እየተከበረ ነው
በዓሉ ከዋዜማው አንስቶ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት እንዱ ነው
የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለይም ደግሞ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ በዓል ነው።
በዓሉ ከዋዜማው አንስቶ በአደባባይ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት እንዱም ነው።
አል ዐይን አማርኛ የመስቀል በዓል ለምን ይከበራል? በዓሉስ ምን ማለት ነው? ሲል የሀይማኖት አባት እና የማህበረሰብ ሳይንስ ምሁር ጋር ቆይታ አድርጓል።
ቀሲስ ታምራት ሺፈራው በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት መስቀል በዓል ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ብዙ ትርጉም ዓለው ብለዋል።
በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ነጻ ለማውጣት ወደ ምድር በመምጣት ተሰቅሎ ጨለማን ወደ ብርሃን የቀየረበት ነው ብለዋል።
እየሱስ ክርስቶስ የተቀለበት መስቀል በአረማውያን ለረጅም ዘመናት ተደብቆ ቆይቶ ነበር የሚሉት ቀሲስ ታምራት እስራኤላዊዋ ንግስት እሌኒ በእግዚያብሄር መሪነት ይህን መስቀል በ16 በጭስ እየተመራች እውነተኛውን መስቀል ያገኘችበት ዕለት ነው፣ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት ደግሞ መስቀሉ የተገኘበት ዕለት መስከረም 17 እንዲከበር በወሰኑት መሰረት በዓሉ ይከበራል ሲሉም አክለዋል።
በመሆኑም ምዕመናን በየዓመቱ መስከረም 16 ደመራን የሚያከብሩት የንግስት እሌኒ በጭስ ታግዛ መስቀሉን ያገኘችበትን ሁነት ለማሰብ ነው ሲሉም ቀሲስ ታምራት ነግረውናል።
ይህ እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሹ በኢትዮጵያ ወሎ ውስጥ ግሸን ደብረ ከርቤ እንደሚገኝ የሚናገሩት ቀሲስ ታምራት ቀሪው የመስቀሉ ክፍል በተለያዩ ሀገራት እንደሚገኝ ይነገራልም ብለዋል።
ይህ መስቀል ከተገኘ 5 ሺህ 500 ዓመታትን እንዳስቆጠረ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታምናለች የሚሉት ቀሲስ ታምራት፤ መስቀሉ በእስራኤል ውስጥ ጎለጎልታ ተብሎ በሚጠራው ተራራ ላይ መገኘቱን ይናገራሉ።
መስቀል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኞች አዳኝ ወይም ብርሃን ተደርጎ እንደሚቆጠርም ቀሲስ ታምራት ነግረውናል።
የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ መሰረት ቢኖረውም ከቦታ ቦታ በተለያየ መንገድ የማህበረሰቡን አንድነት በሚያስጠብቅ መልኩ ይከበራል ያሉን ደግሞ የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያው እና የ"ክብረ በዓላት፣ ሀይማኖት እና ባህል" መጽሀፍ ጸሀፊው መላኩ ጌታቸው ናቸው።
በዓሉ በሰሜን ኢትዮጵያ፣ መሀል እና ደቡብ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ሀይማኖቱን እና የማህብረሰብ ማንነትን መሰረት በማድረግ እንደሚከበርም ባለሙያው አክለዋል።
የመስቀል በዓል በአዲግራት፣ ዋግኽምራ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ አዊ፣ ሸዋ፣ ሺናሻ፣ ወለጋ እና በደቡብ አካባቢዎች በተለያየ መንገድ የህዝቡን አንድነት እና ለፈጣሪ ምስጋናን በማቅረብ እንደሚከበር አጥኚው ተናግረዋል።
የመስቀል በዓል በተለይ በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በጉራጌ፣ ሀድያ፣ ሸካ፣ የም እና ጋሞ ለየት ባሉ መንገዶች ይከበራል የሚሉት አጥኚው በዓሉ ለስራ የተጠፋፉ ቤተሰቦች የሚገናኙበት፣ ልጆች ለወላጆች ስጦታዎች ሰጥተው ምርቃት የሚያገኙበት፣ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና ሌሎች በረከቶችን የሚያገኙበት ነውም ብለዋል።
በአዲግራት የመስቀል በዓል ደመራው መስከረም 16 ተዘጋጅቶ በማግስቱ ጥህሎ በመብላት የሚጀመር ሲሆን በዋግኽምራ ደግሞ ከደመራው በኋላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች በየቤቱ እየዞሩ የምስራች ዝማሬዎችን በማቅረብ ስጦታዎችን በማግኘት ይከበራል ብለዋል።
በወልቃይት፣ ጎንደር፣ ጎጃም ደግሞ አስጨናቂ የክረምት ወራት ማለፋቸውን ተከትሎ የበቆሎ እሸት የሚቀመስበት፣ ለፈጣሪ ምስጋናዎች የሚቀርብበት ፣ ለቀጣዩ የመኸር ወቅት መልካም ምኞች የሚቀርብበት በዓል እንደሆነም ባለሙያው ነግረውናል።
በተለይም በአዊ ጎንደር እና በጎጃም ወጣቶች የተቦካ የስንዴ አልያም የጤፍ ሊጥ ወደ ደመራ ቦታዎች በማምጣት እና በደመራው እሳት እንዲበስል በማድረግ "ድፉኝ" አልያም "ጉዝጉዝ" ወይም "ርሚጦ" የተሰኘውን ምግብ እንደሚመገቡም የማህበረሰብ አጥኚው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እና ዙሪያ ደግሞ የመስቀል በዓል የውጭ ሀገራት ጎብኚዎችን በሚስብ መንገድ በመስቀል አደባባይ እና በየአካባቢው የህዝቡን አንድነት በጠበቀ መንገድ ይከበራል ተብሏል።
የመስቀል በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ይከበራል ያሉን የማህበረሰብ አጥኚው በደቡብ ኢትዮጵያ ሰዎች እንደ አቅማቸው በሬ አልያም ሌሎች እንስሳቶችን በማረድ ያከብራሉም ብለዋል።
በምዕራብ ኢትዮጵያ በተለይም በወለጋ ደግሞ ወንዶቹ ወደ ወንዝ በመሄድ ቄጠማ እና የእርድ በሬ የማዘጋጀት ባህል እና በዓል አከባበር እንዳላቸውም አጥኚው ተናግረዋል።
"ጆልቡልቲ" በተሰኘ ዘፈን የመስቀል በዓላቸውን የሚያደምቁት ወለጋዎች ደመራው በአካባቢው ባሉ ትልቅ ሽማግሌዎች ምርቃት በኋላ ተለኩሶ ይከበራልም ተብሏል።
በአጠቃላይ የመስቀል በዓል አከባበር መነሻው ሀይማኖታዊ መሰረት ቢኖረውም በሰሜን ኢትዮጵያ እሸት በመቅመስ እና ስለ ቀጣዩ የመኸር ወቅት ለሰብል ስብሰባ ተስፋ በመሰነቅ ሲከበር በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍሎች ደግሞ በብዛት በእንስሳት እርድ ደምቆ ይከበራል ተብሏል።
እርስዎ ባሉበት አካባቢ በዓሉን እንዴት ይከበራል?
መልካም የመስቀል በዓል ይሁንልዎ