አራት ምዕራባውያን ሀገራት ተመድ በሱዳን በተፈጸሙ ግፎች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ ሊጠይቁ ነው
በሱዳን ባለፈው ሚያዝያ ወር በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ደም መፋሰስ፣ ግጭት እና መፈናቀሎች ተባብሰው ቀጥለዋል
ሀገራቱ በሱዳን የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ሶስት ባለሙያዎች ያሉት የእውነት አፈላላጊ ቡድን እንዲቋቋም ይፈልጋል
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ እና ጀርመን የተመድ የሰብአዊ መብቶች ካውንስል በሱዳን ተፈጽመዋል የሚባሉ ግፎችን የሚያጣራ ምርመራ እንዲጀምር የሚጠይቅ ምክረሃሳብ ሊያቀርቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በሱዳን ባለፈው ሚያዝያ ወር በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ደም መፋሰስ፣ ግጭት እና መፈናቀሎች ተባብሰው ቀጥለዋል።
በግጭቱ በከፍተኛ መጠን ከተጠቁ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ዳርፉር ግዛት እንዷ ነች። በግዛቷ ብሔርን መሰረት ባደረገ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ገድለዋል።
በንጹሃን ላይ ጥቃት በማድረስ የሚከሰሰው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አልፈጸምኩም ሲል አስተባብሏል። ግጭቱ የውስጥ ጉዳይ ነው የሚለው የሱዳን መንግስትም ንጹሃንን በመግደል እጁ እንደሌለበት ገልጿል።
በምዕራባውያን ሀገራት የቀረበው ምክረሃሳብ በሱዳን ባለፉት አምስት ወራት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ሶስት ባለሙያዎች ያሉት የእውነት አፈላላጊ ቡድን እንዲቋቋም ይፈልጋል።
ባለሙያዎቹ የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንዲመዘግቡ እና 47 አባላት ላሉት ምክርቤት በቃል እና በጹሁፍ እንዲያቀርቡ በምክረሃሳብ ሰነድ ተጠቅሷል።
ጦርነቱን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት በአሜሪካ እና ሳኡዲአረቢያ እንዲሁም በኢጋድ የደረጉተሰ ሙከራዎች ውጤት አላስገኙም።