በሱዳን ያለው አለመረጋጋት ኢትዮጵያን መጉዳቱ እንደማይቀር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ
የጸጥታ እና የሰብዓዊ ጉዳዮችን የሚከታተል ግብረ ሀይል መቋቋሙንም ሚኒስቴሩ ገልጿል
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ሱዳን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ሳትመለስ አይጀመርም ተብሏል
በሱዳን ያለው አለመረጋጋት ኢትዮጵያን መጉዳቱ እንደማይቀር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም በወቅታዊ እና መደበኛ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በጎረቤት ሀገር ሱዳን የተጀመረው ጦርነት ጉዳይ የመግለጫቸው ዋነኛ ማጠንጠኛ የነበረ ሲሆን በዚህ ጉዳይ ዙሪያም ከጋዜጠኞች በርከት ያሉ ጥያቄዎች ለቃል አቀባዩ ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም በሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያን ደህንነት ጉዳይ፣ የተሸለ ደህንነት ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ስለሚገቡ ዜጎች፣ የሱዳን አለመረጋጋት በጎረቤት ሀገራት ላይ ሊኖራቸው ስለሚችሉ ጉዳቶች እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፤
አምባሳደር መለስ በምላሻቸው እንዳሉት ሱዳን ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን፣ በካርቱም ያለው የኢትዮጵያ ኢምባሲ እና ገዳሪፍ ባለው ቆንስላ ቢሮ አማካኝነት አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ተመድ በሱዳን ያለው ጦርነት ቶሎ ካልቆመ ወደ ጎረቤት ሀገራት የመዛመት እድል አለው ሲል ማስጠንቀቁን ተከትሎ ይህ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ጉዳት ሊያስከትል ይችላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም “ጎረቤት ሀገር የተፈጠረ ማንኛውም ነገር አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል፤ ጦርነቱ በሱዳን የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ይጎዳል፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ዜጎችን ቁጥር ይጨምራል፣ ይህም በኢትዮጵያ ላይ የደህንነት ስጋቶችን እና የሰብዓዊ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ቁጥር በማናር ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራል“ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአጼ ሀይለስላሴ አስተዳድር ጊዜ ጀምሮ የሱዳናዊያንን አምባ ስታብስ ቆይታለች የሚሉት ቃል አቀባዩ አሁንም ያንን እያደረገች እንደሆነም አክለዋል፡፡
አምባሳደር መለስ በሱዳን ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መቀነስ ዓላማ ያደረገ ግብረ ሀይል እንደተቋቋመም ጠቁመዋል፡፡
ይህ ብሔራዊ ግብረ ሀይልም የሰብዓዊ ስጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ለመደገፍ እና በጦርነቱ ምክንያት የደህንነት ስጋት በኢትዮጵያ ላይ እንዳይደርስ ሁኔታዎችን የሚከታተል መሆኑንም አምባሳደር መለስ ተናግረዋል፡፡
በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው የሶስትዮሽ ውይይት በሱዳን ወቅታዊ ችግር ምክንያት ሊቀጥል አይችልም ያሉት አምባሳደር መለስ ካርቱም ወደ ቀድሞ ሰላሟ ስትመለስ እንደሚቀጥልም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ 50 ሺህ ኩንታል ስንዴ በኢትዮጵያ ኤይድ አማካኝነት ለሱዳን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወሳል፡፡