"ኢትዮጵያ፤ አሜሪካ ህወሓትን በይፋ እና በአግባቡ ታወግዛለች ብላ እንደምጠብቅ ገልጫለሁ"- አቶ ደመቀ መኮንን
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጄፋሪ ፊልትማን ጋር ተወያይተዋል
አቶ ደመቀ ህወሓት "ይህን ሁሉ ጥፋትና የሀገር ክደት ሲፈጽም የአሜሪካ መንግስት ድርጊቱን እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚመጥን ደረጃ" አለማውገዙንና ጥፋቱን የሚያጋልጥ ምላሽ አለመስጠቱን ተናግረዋል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ጋር ተወያዩ፡፡
የሁለቱን አገሮች ረዥም ታሪካዊና በጋራ ጥቅሞችና ዕይታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ባወሱበት በዚህ ውይይት አቶ ደመቀ "ወራሪ ሀይል" ያሉት ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጀምሮ አሁን ያለበትን ዝርዝር ሁኔታን አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአማራና አፋር ክልል በፈፀመው "ግልፅ ወረራ፣ ዘረፋ፣ ግድያ" ማንኛውንም ዓይነት ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥፋቶችን እያካሄደ ይገኛልም ብለዋል።
ህወሓት "ይህን ሁሉ ጥፋትና የሀገር ክደት ሲፈጽም የአሜሪካ መንግስት ድርጊቱን እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነትበሚመጥን ደረጃ" አለማውገዙንና ጥፋቱን የሚያጋልጥ ምላሽ አለመስጠቱንም ነው አቶ ደመቀ የተናገሩት።
ከዚህ አንጻር ከአሜሪካ ገንቢ ሚናን እንደሚጠብቁ ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ከማፍረስ ጀምሮ ቀጠናውን የሚያናጋ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል" ሲሉ ስለማሳሰባቸውም አል ዐይን አማርኛ ከውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አምባሳደር ጄፋሪ ፊልትማን በበኩላቸው የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሃት ላይ ያለውን አመለካከት በውል እንደሚረዱ ገልጸዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላት ፖሊሲ መሠረቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ሠላም እና አንድነት በማስጠበቁ፣ በማረጋገጡ እና በማስቀጠሉ ላይ የተመረኮዘ መሆኑንና የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በነዚሁ መሠረታዊ መልህቆች ላይ ተመስርቶ እንደሚቀጥል ገልፀዋል እንደ ቃል አቀባይ ጽህፈት ።ቤቱ ገለጻ
ፌልትማን አክለውም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ቀጠናዊ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ መጠበቁንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡
አምባሳደር ፌልትማን በጅቡቲ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው እና ከፕሬዝዳንት ኦማር ጉሌ ጋር መክረው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሚታወስ ነው።
ልዩ መልዕክተኛው ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበርም አይዘነጋም ።