"በሱዳን የተወሰደው ግዛታችን በየትኛውም መመዘኛ ይመለሳል" - አቶ ደመቀ መኮንን
ሱዳን ለህወሓት መሰረት መሆኗ እንደ መውጋት እንደሚቆጠርም አቶ ደመቀ ተናግረዋል
ሱዳን የህዝብ ስብጥርን (ዴሞግራፊ) ለመቀየር መሰረተ ልማትን እየገነባች ነውም ተብሏል
በሱዳን የተወሰደው የኢትዮጵያ ግዛት "በየትኛውም መመዘኛ" እንደሚመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ኢትዮጵያ ያላት የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የተነሱ ሲሆን የኢትዮጵያ እና ሱዳን አሁናዊ ግንኙነት ላይም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡
አቶ ደመቀ ሱዳን፤ ኢትዮጵያ በሰሜን ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅማ ወረራ መፈጸሟን አንስተዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት ከመውረር ባለፈ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማፈናቀሏንና የንብረት ውድመት ማድረሷንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ፤ሱዳን ያለባትን ውዝፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ እንድትከፍል ጠየቀች
ሱዳን በወረራ በያዘችው መሬት ላይ የህዝብ ስብጥርን (ዴሞግራፊ) ለመቀየር በማሰብ መሰረተ ልማትን እየገነባች ነው ያሉት አቶ ደመቀ ድርጊቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ ክፉኛ እንዳበሳጨ ገልጸው ኢትዮጵያ ችግሩ በሰላም ይፈታል ብላ እየሰራች እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህንን የሱዳንን ድርጊት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ ለአፍሪካ ሕብረትና ለሌሎችም ማሳወቋን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ "ወረራው አደገኛ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ" በሯን ለሰላም ክፍት አድርጋ እየጠበቀች ትገኛለች ብለዋል፡፡
ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትወዛገብበት የአል ፋሽቃ የድንበር አካባቢ የገነባቻቸውን መሰረተ ልማቶች አስመረቀች
ኢትዮጵያ በሰሜን ካጋጠማት ችግር ጋር ተያይዞ ሱዳን ባለችበት እንድትቆይ ንግግር መደረጉንና ኢትዮጵያም ይህንኑ ማድረጓን የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን ኢትዮጵያን አቋም ከማበረታታት ባለፈ የካርቱምን ድርጊት አለማውገዙን አስታውቀዋል፡፡
የሱዳን መንግስት ድንበር ጥሶ ወረራ ከመፈጸሙ ባለፈ ለህወሓት መሰረት በመስጠት ወደ ኢትዮጵያ ጥቃት እንዲሰነዘር እያደረገ መሆኑንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ይህ "የመውጋት ያህል" እንደሆነ የገለጹት አቶ ደመቀ ይህንንም እንዲያውቁት አድርገናልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ፤ ከሱዳን ጋር ያለው ጉዳይ በሰላም እንዲፈታ ማድረግ ያለባትን ሁሉ እያደረገች እንደምትቀጥል አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ "ግዛታችን ይመለሳል" ሲሉም አቶ ደመቀ ተናግረዋል፡፡ ከከፋ ጉዳት መለስ ባለ ሰላማዊ መልክ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ ጥረቱ እንደሚቀጥልና መንግስትም ይህንን እየተከታተለ እንደሆነም ነው አቶ ደመቀ ለምክር ቤቱ የተናገሩት፡፡