“አንዳንድ ተዋንያን በሰብዓዊ ዕርዳታ ሽፋን ሽብርተኞችን ለማስታጠቅ መሞከራቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒ ማስረጃዎች አሉ”- አቶ ደመቀ መኮንን
በሰብዓዊነት ሽፋን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት አቶ ደመቀ ገልጸዋል
“ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ይበልጥ የሚያባብስ ጫና ሳይሆን ድጋፍ ነው የሚያስፈልጋት” ብለዋል
በትግራይ ያለውን ሁኔታ በመጠቀም የተለያዩ አካላት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ሀገሪቱን እንዳሳዘነ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቪዲዮ ባስተላፉት መልእክት፣ “አሁን የሚያስፈልገን ጠንክራ ድጋፍ ነው፤ የኢትዮጵያን ህዝቦችና የግዛት አንድነት አንዲሁም ትስስርን በሰብዓዊነት ሽፋን ዝቅ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን ከፍ ለማድረግ፣ ማህበራዊ ትስስርን መልሶ ለመገንባት እና መሰረታዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከሁሉም አጋሮቿ ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል።
በመሆኑም “ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ያለውን ሁኔታ ይበልጥ የሚያባብስ ጫና ሳይሆን ከወዳጅ እና አጋር ሀገራት ድጋፍ ነው የሚያስፈልጋት” ብለዋል።
የተለያዩ አካላት ጫና ለመፍጠር እያደረጉት ያለው ተግባር ኢትዮጵያን እንዳሳዘናት የጠቀሱት አቶ ደመቀ፣ “ይህ የወዳጅነት ተግባር አይደለም” በማለት የኢትዮጵያ መንግስትም እንዲህ አይነቱን አካሄድ እንደማይቀበል ነው ያስታወቁት።
ከዚህ አንፃር በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወገኖች በሰብዓዊነት ሽፋን የኢትዮጵያን ህዝቦች እና የግዛት አንድነት እንዲሁም ትስስር ለማዳከም ተልእኮ ይዘው ሲሰሩ ማየት “የሚያሳዝን ተግባር ነው” ያሉት አቶ ደመቀ፤ እነዚህ ግለሰቦች እና አጋሮቻቸው ከዚህ ተግበራቸው እንዲታቀቡም አሳስበዋል።
“ኢትዮጵያ በራሷ ዜጎች ላይ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያነት እየተጠቀመች ነው” በሚል በሀገሪቱ ላይ የተለጠፉ ክሶች “መሰረተ ቢስ ናቸው፤ እንደዚህ አይነት ክሶች በምንምን ስሌት ሰላምን እና መረጋጋትን ለመፍጠር አይረዱም” ብለዋል።
መንግስት እስካሁን በትግራይ ክልል በመጀመሪያ ዙር ለ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ ፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙርም ወደ 5.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ማድረጉን አቶ ደመቀ አስታውሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ያለውን ፍላጎት እና ቁርጠኝነት ከማሳየቱም ባሻገር የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ አካላት በክልሉ በነጻነት እንዲሰሩ የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋቱንም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ “አንዳንድ ተዋንያን በሰብዓዊ ዕርዳታ ሽፋን የሽብርተኞችን ቡድን ለማስታጠቅ መሣሪያዎችን በድብቅ ለማስገባት መሞከራቸውን የሚያመለክቱ ተዓማኒ ማስረጃዎች እንዳሉን እዚህ ላይ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል አቶ ደመቀ መኮንን፡፡
“በትግራይ ክልል ውስጥ ስላሉት ተግዳሮቶች ግዙፍነት ጥርጥር የለውም” ያሉት አቶ ደመቀ፣ እያንዳንዱን የሰብዓዊ ድጋፍ ፈላጊ በመድረስ ችግሩን መቅረፍ የሚቻለው ከመንግስት ጋር በመስራት እንደሆነም ነው የጠቆሙት፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለገዛ ዜጎቹ የሚኖረውን ኃላፊነት እና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕጎች ላይ የሚኖረውን ግዴታ በሚገባ ያውቃል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አቶ ደመቀ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት የተቸገሩትን ለመደገፍ ከሀገር ውስጥ ሀብት በማሰባሰብ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ ቢሆንም ሀብቱ ውስን መሆኑን ጠቅሰው፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እና አብሮነት የበለጠ ወሳኝ የሚሆነው ለዚሁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የእርዳታ እጃቸውን ለዘረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አዎንታዊ እና ገንቢ በሆነ መልኩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ከሆኑት አጋሮች ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ እና ቁርጠኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት በትናንትናው ዕለት ባወጣው ሪፖርት ፣ በትግራይ ክልል 350 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ለርሃብ መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡ ዩኤስአይዲ ከተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተቋማት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ባደረገው ውይይት የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ በመጥቀስ መንግስትን ተችቷል፡፡ “ኢትዮጵያ በራሷ ዜጎች ላይ ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያነት እየተጠቀመች ትገኛለችም” ብሏል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት በተከታታይ በሚሰጣቸው መግለጫዎች ይህን ትችት አስተባብሏል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ በሰብዓዊ ድጋፍ ሽፋን እየተንቀሳቀሱ ለሕወሓት የጦር መሣሪያ የማድረስ ስራ የሚሰሩ ድርጅቶች ስለመኖራቸው መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡