በቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ምን ይመስል ይሆን?
801 ቢሊዮን ብር የተመደበለት የ2016 በጀት ዓመት እድሎች እና ስጋቶቹ ምን ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስለ ቀጣዩ ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ቢሁኔዎችን አስቀምጠዋል
የ2015 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ ቀናቶች ብቻ ቀርቶታል፡፡
ከሀገር ውስጥ የሰሜኑ ጦርነት፣ በየቦታው የተፈጠሩ አለመረጋጋቶች፣ ህገ ወጥ ንግድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የፈተኑ የሀገር ውስጥ ፈተናዎች የነበሩ ሲሆን የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት፣ የነዳጅ ዋጋ መናር እና ዓለም አቀፍ ንግድ መቀዛቀዝ ተጨማሪ ጫናዎች ነበሩ፡፤
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ ቀጣዩ የ2016 በጀት ዓመት መወያየት የጀመረ ሲሆን በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረበለትን የ801 ቢሊዮን ብር ረቂቅ በጀት ላይም መወያየት ከጀመረ አንድ ሳምንት ሆኖታል፡፡
አልዐይን አማርኛ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2016 ዓመት ምን ምን እድሎች እና ስጋቶች ይኖሩታል? ኢኮኖሚውስ ምን ሊመስል ይችላል? የተመደበው በጀትስ በኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት ሚና ይኖረዋል? በሚል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡
አቶ መቆያ ከበደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ለ2016 በጀት ዓመት የተዘጋጀው ረቂቅ በጀት ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በብዙ ጉዳዮች መፈተኑን እንደሚቀጥል ያሳያል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ መቆያ ገለጻ የመንግስት የበጀት ጉድለት ከ231 ቢሊዮን ብር ወደ 281 ቢሊዮን ብር ማደጉ እና የበጀት ጉድለቱን ሊሞላ ያሰበበት መንገድ ሲታይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋጋ ግሽበት እንዲፈተን እና በነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ግብር እንዲጣል የሚያደርግ ነው፡፡
መንግስት የገጠመውን የበጀት ጉድለት ለመሙላት ከባንኮች ከፍተኛ ብድር መውሰዱ እና ብር ማተሙ አይቀርም የሚሉት አቶ መቆያ፥ ይህ ሲሆን ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ አሁን ካለበት እስከ 30 በመቶ ሊጨምር ይችላልም ብለዋል፡፡
የመንግስት የበጀት ጉድለት በጨመረ ቁጥር መንግስት ጫናውን ለመቀነስ ሲል ወጪ ወደ መቀነስ ስለሚሄድ የስራ እድል ፈጠራ መቀነስ፣ የመሰረተ ልማት አለመጠናቀቅ፣ የንግድ እና ሌሎች ለኢኮኖሚው አነቃቂ የሆኑ ስራዎች እየተስተጓጎሉ መሄዳቸው እንደማይቀርም ጠቅሰዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቆም፣ የሕገወጥ ማእድናት ግብይትን ለመቆጣጠር የተጀመሩ ስራዎች የቀጣይ ዓመት ኢኮኖሚያችን ላይ አወንታዊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ የሚሉት አቶ መቆያ የብድር ጫና እና የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር መላላትን ደግሞ በስጋትነት አስቀምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ለምን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጠማቸው?
በዩኒቲ ዩንቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ፋሲል ጣሰው በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ዓመታዊ በጀቷን ከ12-15 በመቶ እያሳደገች መምጣቷን ተናግረዋል፡፡
የቀጣይ ዓመት ረቂቅ በጀት ሲታይ ግን የሁለት በመቶ ብቻ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቀሱት መምህር ፋሲል አብዛኛው በጀት ደግሞ ለመንግስታዊ ወጪ የሚውል መሆኑ ኢኮኖሚያው ላይ ተጫማሪ ጫና መፍጠሩ እንደማይቀር አክለዋል፡፡
መንግስት በረቂቅ በጀት እቅዱ ላይ ያላከተተው ተጨማሪ በጀት ሊኖር እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት መምህር ፋሲል በተለይ "ለቅንጦት ፕሮጀክቶች" ማስፈጸሚያ ሌላ በጀት ሊኖረው ይችላልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2016 በጀቷ ላይ ከዚህ በፊት ለተበደረቻቸው ብድሮች ክፍያ 160 ቢሊዮን ብር ለመክፈል በረቂቅነት መያዟን የጠቀሱት ባለሙያው ይህም ኢኮኖሚውን የባሰ እንዲጎዳ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ላይ ሲደርሱ የነበሩ የዲፕሎማሲ ጫናዎች አሁን ላይ ቀለል ማለታቸው፣ በእርዳታ መልክ የሚሰጡ ገንዘቦች እየጨመረ መምጣቱ፣ የጸጥታ ሁኔታዎችን እየተቆጣጠረ መምጣቱ ኢኮኖሚው በተወሰነ መንገድ ከባሰ ጉዳት ሊጠብቁት የሚችሉ መልካም ሁኔታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉም መምህር ፋሲል ጠቅሰዋል፡፡
መንግስት በሚቀጥለው ዓመት ሊኖረን የሚችለውን ኢኮኖሚ የተሻለ ለማድረግ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የቅንጦት ፕሮጀክቶችን በማቋረጥ ሀብት ሊፈራባቸው በሚችሉ ስራዎች ላይ ማተኮር እና ኢ- መደበኛ የኢኮኖሚ መስኮች እንዳይጎዱ ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባም ባለሙያው ምክረ ሀሳባቸውን አስቀምጠዋል፡፡