የ2016 በጀት 801 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ተወሰነ
ከ2015 በጀት ጋር ሲነጻጸር 15 ቢሊዮን ብር ገደማ ብቻ የሚበልጠው ረቂቅ በጀቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል
አዲሱ በጀት በሰሜኑ ጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከመገንባት አኳያ የተቃኘ ነው ተብሏል
የሚንስትሮች ምክር ቤት በ21ኛ መደበኛ ስብሰባው የ2016 ረቂቅ በጀትን አጽድቋል።
ምክር ቤቱ ባካሄደው ስብሰባ የፌዴራል መንግስት የተለያዩ የልማት እቅዶችን፣ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫዎች አጢኖና የደህንነት ጉዳዮች ተመልክቶ የሚቀጥለው ዓመት በጀት መዘጋጀቱ ተነግሯል።
"[የ2016 በጀት] በአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ የተቀመጡ ግቦችን ታሳቢ በማድረግ፣ የሀገር ደህንነት ከማስጠበቅ፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ከመርዳት፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከማቋቋም፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ሽግግርን አቅጣጫዎችና ዓላማዎች ከማሳካት አኳያ የተቃኘ" ሲል ስለ ረቂቅ በጀቱ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ከዚህ ባሻገርም በጀቱ የ2016 እስከ 2020 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ ነው ተብሏል።
የ2016 በጀት ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች 369.6 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 203.9 ቢሊዮን፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 214.07 ቢሊዮን፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ ብር 14 ቢሊዮን በጠቅላላው ብር 801.65 ቢሊዮን ብር ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል።
ምክር ቤቱ በቀረበው በጀት ላይ ተወያይቶ 'ግብዓቶችን በማከል' ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
ሰኔ 30 የሚጠናቀቀው የ2015 ዓመት በጀት 786.6 ቢሊዮን ብር ነው።