ባንኮች ከፍ ያለ ካሽ ገንዘብ ለማውጣት ለሚጠይቋቸው ደንበኞቻቸው አገልገሎቱን እየሰጡ አይደለም
የኢትዮጵያ ባንኮች ለምን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ገጠማቸው?
ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ባንኮች ለደንበኞቻቸው በተለይ መጠኑ ከፍ ያለ ካሽ ገንዘብ ለማውጣት ለሚጠይቋቸው ደንበኞቻቸው አገልገሎቱን እየሰጡ አይደለም።
አል ዐይን አማርኛ በአዲስ አበባ ተዘዋውሮ ቅኝት ባደረገባቸው የተለያዩ ባንክ ቅርንጫፎች በባንክ ባለሙያዎች እና ደንበኞች መካከል ንትርኮች መኖራቸውን ታዝበናል።
ከባንክ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጆች እና አገልገሎት ፈላጊዎች ጋር ባደረግነው ቆይታም ከጥቂት ባንኮች በስተቀር አብዛኞቹ ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንደገጠማቸው እና ብድር መስጠት በጊዜያዊነት ማቆማቸውን ነግረውናል።
- ኢትዮጵያ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከሟ አይቀሬ መሆኑን ኢኮኖሚስቶች ተናገሩ
- የፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ሀብት 2 ነጥብ 91 ትሪሊዮን ብር መድረሱን ብሔራዊ ባንክ ገለጸ
አገልገሎት ፈልገው ወደ ባንኮች ያመሩ ተገልጋዮችም ከባንኮች በተለይም በርከት ያለ ጥሬ ገንዘብ ለማውጣት ሲጠይቁ ባንኮች እንደሚያጉሏሏቸው፣ ብድር ለመውሰድ ሲጠይቁም ብድር ለጊዜው መቆሙን እንደሚነግሯቸው ጠቅሰውልናል።
አል ዐይን አማርኛ አብዛኞቹ ባንኮች ለምን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሊገጥማቸው ቻለ ብድርስ ለምን ሊከለክሉ ቻሉ ሲል የኢኮኖሚ ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
አቶ ዋሲሁን ኢኮኖሚስት የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው፤ እሳቸው እንዳሉት ባንኮች ላጋጠማቸው የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና ብድር ክልከላ አራት ቢሆኔዎችን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ዋሲሁን አስተያየት ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሊያጋጥማቸው የሚችለው ወቅቱ የበጀት መዝጊያ እና አመታዊ ግብር የሚከፈልበት ወቅት በመሆኑ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከግል ባንኮች ወደ መንግስታዊ ባንኮች ስለሚዞሩ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት በገበያው ውስጥ ባለው ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ መሰራጨት ምክንያት መሆኑን ብሔራዊ ባንክ በመረዳቱ እና ይህንን ለማስተካከል የተወሰደ እርምጃ ሊሆን ይችላል በሚል በባንኮች ላጋጠመው የጥሬ ገንዘብ እጥረት በሁለተኛ ምክንያትነት ተጠቅሷል።
ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ በገበያው ውስጥ ያለው የጥሬ ገንዘብ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ባንክ እንዲመለስ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦቶችን እና ብድሮችን መከልከል በሚል በባንኮች እና ብሔራዊ ባንክ ውይይት መሰረት የተወሰደ እርምጃ ሊሆን እንደሚችልም አቶ ዋሲሁን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አራተኛው ምክንያቶ ደግሞ ከባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር ወስደው በስራ ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሌሎች የንግድ ተቋማት በብዙ ምክንያቶች ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ባለመቻላቸው እና ብድሮቻቸውን በሚገባ መክፈል ባለመቻላቸው ባንኮችን ለጥሬ ገንዘብ እጥረት ሊዳርግ ይችላልም ተብሏል።
ባንኮች የጥሬ ገንዘብ እና ብድር የከለከሉት ብሔራዊ ባንክ ዘግይቶም ቢሆን ለዋጋ ግሽበቱ እና ኑሮ ውድነቱ ትክክለኛ እርምጃ በመውሰዱ መሆኑን እርግጠኛ ነኝ ያሉን ደግሞ ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራ ሽታሁን ናቸው።
እንደ አቶ ሸዋፈራ ገለጻ ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው እና መሸከም ከሚችለው በላይ የሆነ ገንዘብ ወደ ገበያው በተለያዩ መንገዶች እንዲገቡ ሲያደርግ ነበር።
በተለይም መንግስት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲያትም መቆየቱ፣ ለኢኮኖሚው አጋዥ ባልሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ሲወጣ መቆየቱ እና ጦርነቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መጉዳታቸውን አቶ ሸዋፈራ ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያትም ዜጎች ላልተገባ የዋጋ ግሽበት ከመጋለጣቸው ባለፈ ባንኮችም በገፍ ብድር ሲሰጡ መቆየታቸው በኢኮኖሚው ላይ ተጨማሪ እና ውስብስብ ጉዳቶች ማድረሱን አቶ ሸዋፈራ ጠቁመዋል።
ብሔራዊ ባንክ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ላለመጉዳት ሲል ውሳኔውን በይፋ ለህዝብ አለማሳወቁን አረዳለሁ የሚሉት ባለሙያው የጥሬ ገንዘብ ክልከላው በተጠና እና ለተወሰነ ጊዜ የሚተገበር ከሆነ የዋጋ ግሽበቱን እንደሚያረጋጋውም ነግረውናል።
የባንኮች ውሳኔ ደንበኞቻቸውን ቢያበሳጭም እንደ ሀገር ግን የዋጋ ግሽበቱን በማረጋጋት ይጠቅማል፣ የብድር ክልከላው አንገብጋቢ የሆኑ ስራዎችን በማይጎዳ መልኩ ሊተገበሩ እንደሚገባም አቶ ሸዋፈራ አሳስበዋል።