የኤክሳይስ ታክስን በድጋሚ ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውይይት ተካሂዶበታል
በ2012 ዓ.ም የተሻሻለውና በተሽከርካሪዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ የሚጥለው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ በድጋሚ እንዲሻሻል ባለፈው ጥር ወር ላይ ረቂቁ ለህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት ቀርቧል።
መንግስት የአዋጁን ስኬትና ጉድለት ማጥናቱን ገልጾ፤ "የታክሱ ምጣኔዎች በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ ጫና ማሳደራቸው፣ የተጋነነ የክፍያ ምጣኔ መገኘትና ገቢን ለማሳደግ አዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል።
አዲሱ የኤክሳይዝ አዋጅ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
በ2012 ዓ.ም. ተሻሽሎ የጸደቀው አዋጅ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎችና የቅንጦት የተባሉ እቃዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ የጣለ ነበር።
- ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከታገዱ ምርቶች መካከል ዋነኞቹ የትኞቹ ናቸው…?
- በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን የገንዘብ ሚኒስቴር ገለፀ
በአዲሱ ኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ላይ ታክስን በጊዜያዊነትና ሙሉ ለሙሉ ከማንሳት ጀምሮ የምጣኔ ማሻሻያና አዲስ ለውጥ ተደርጓል።
ማሻሻያ የተደረገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች:-
¤ ተሽከርካሪዎች ላይ ተጥሎ የነበረው 30 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡
በአዲሱ አዋጅ እስከ 1300 ሲሲ ያላቸው አዲስ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ለማበረታታት ተጥሎ የነበረው 30 በመቶ ወደ 5 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡
በአራተኛ ምድብ የተከፈሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ከ1500 ሲሲ በታች የሆኑት 10 በመቶ፤ 1501-2500 ሲሲ 20 በመቶ ከ2501-3000 ሲሲ 30 በመቶ እና ከ3000 ሲሲ የሆኑት 60 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፈልባቸዋል።
¤ ተደራራቢ የኤክሳይስ ታክስ የሚከፈልባቸው ምርቶች የተባሉት ንጹህ አልኮልና ስኳር ምጣኔያቸው ዝቅ ተደርጓል።
አልኮል ላይ የተጣለው 60 በመቶ ታክስ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል በአዲሱ ረቂቅ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ስኳር ደግሞ ከ20 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ይደረጋል።
¤ ገቢን ለማሳደግ ከቴሌ ኮሚኒኬሽን አገልግሎት 5 በመቶ የኤክሳይስ ታክስ ለመሰብሰብ ታስቧል።
¤ በ2012ቱ አዋጅ በቪዲዮ ካሜራ ላይ የነበረው 40 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ወደ 10 በመቶ ዝቅ ቢልም በተሻሻለው ታክሱ ተነስቷል።
¤ በቴሌቪዥን ላይ የነበረው 10 በመቶ የኤክሳይስ ታክስም ተነስቷል።
¤ ከ100 ግራም ውስጥ 40 ግራም ወይም የበለጠ “ሳቹሬትድ ስብ” የያዘ የአትክልት እና የእንስሳት ዘይት ላይ የተጣለው ታክስ ለጊዜው ቀሪ እንዲሆን ተደርጓል።
¤ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች፣ ለኢንቨስተሮችና ለአካል ጉዳቶኞች ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ ተደርገው ከነየነበሩ ምርቶች ተነስተዋል።
መንግስት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት፣ በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶችን ፍጆታ ለመቀነስ፣ ከቅንጦት እቃዎች ገቢ ለመሰብሰብ እንዲሁም አካባቢ ደህንነት ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ኤክሳይስ ታክስን ይጥላል፡፡