አንድ ቶን ስንዴ ወደ ውጭ ሲላክ 101 ነጥብ 4 ዶላር ታክስ እንዲከፈል የሩሲያ መንግስት ወስኗል
የሩሲያ መንግስት ወደ ውጭ በሚላከው ስንዴ ላይ የታክስ ጭማሪ ማደረጉን የሀገሪቱ ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ፤ ከሀገሪቱ ወደ ውጭ በሚላክ ስንዴ ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረጉን የገለጸ ሲሆን ይህም በዚህ ሳምንት ተግባራዊ ይደረጋል ብሏል፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ቶን ስንዴ ወደ ውጭ ሲላክ 101 ነጥብ 4 ዶላር እንዲከፈል መንግስት ወስኗል።
የታክስ ጭማሪም በዚህ ሳምንት ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ የተደረገ ሲሆን፤ የወጣው የዋጋ ተመን ለአንድ ሳምንት የሚያገለግል መሆኑም ተጠቅሷል።
ሞስኮ ከስንዴ በተጨማሪም ወደ ውጭ ሀገራት የሚላኩ የበቆሎ እና ገብስ ምርት ላይ የታክስ ጭማሪ ማድረጓን ገልጻለች።
በተደረገው ጭማሪ መሰረትም አንድ ቶን በቆሎ ወደ ውጭ ሲላክ የሚከፈለው ታክስ 70 ነጥብ 6 እንዲሁም አንድ ቶን ገብስ ወደ ውጭ ሲላክ 75 ነጥብ 4 ዶላር እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል ነው የተባለው።
በስንዴ፣ ገብስና በቆሎ ላይ የተደረገው የታክስ ጭማሪ በምርቶቹም ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያመጣ አመላካች ነውም ተብሏል።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በስንዴ ምርት ላይ ከፍተኛ እጥረት አሊያም የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል ፍርሃቶች መኖራቸው ተገልጿል።
ይህንን ፍርሃር ግምት ውስጥ ያስገቡ ሀገራትና ኩባንያዎችም ስንዴን ለመግዛት የሚደርጉት እሽቅድምድም የስንዴ ዋጋን ሊያንረው ይችላል የሚል ፍርሃት አለ።
በጦርነት ላይ ያሉት ሩሲያ እና ዩክሬን ከፍተኛ ስንዴ አምራቾች ሲሆኑ፤ ሁለቱም የዓለምን 30 በመቶ የስንዴ ሽያጭ ያከናውናሉ።