ኢትዮጵያ በ2 ወራት ከ13 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የኤሌክትሪክ ኃይል መሸጧን አስታወቀች
የኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳን እና ለጅቡቲ መሸጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ
በ2 ወራት ለሱዳንና ለጅቡቲ 232 ነጥብ 76 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ቀርቦላቸዋል
በሁለት ወራት ለሱዳንና ለጅቡቲ ኤክስፖርት ከተደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ከ13 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ሽያጭ መከናወኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በተቀዋሙ የማርኬቲንግና ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት መምሪያ የሽያጭና ደንበኞች አስተዳደር ቢሮ ሥራ አስኪያጁ አቶ ምኒሊክ ጌታሁን እንደገለጹት ባለፉት ሁለት ወራት ለሰዩዳን እና ለጅቡቲ ከቀረበው የኤለክትሪክ ሃይል 13.04 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል።
በዚህም ለሱዳን 112 ነጥብ 36 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት ኃይል በማቅረብ የ5 ነጥብ 61 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለጅቡቲ 120 ነጥብ 39 ሚሊዮን ኪሎ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የ7 ነጥብ 42 ሚሊዮን ዶላር ሽያጭ መከናወኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለጅቡቲ ለማቅረብ በዕቅድ ከተያዘው ኃይል የ12 ነጥብ 29 በመቶ ብልጫ ያለው ኃይል የቀረበ ሲሆን ለሱዳን ደግሞ የዕቅዱን 46 ነጥብ 36 በመቶ ብቻ መሸጥ እንደተቻለ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
ከጅቡቲ የተገኘው ገቢ ግን ከዕቅዱ የ15 ነጥብ 38 በመቶ ብልጫ ያሳየ ነበር ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ከሱዳን ይገኛል ተብሎ ታቅዶ የነበረውን ሽያጭ ማሳካት ያልተቻለው በሁለቱ ወራት የሱዳን የኤሌክትሪክ ኩባንያ ኃይል የመግዛት ፍላጎቱ በመቀነሱ እንደሆነ አቶ ምኒሊክ አስታውቀዋል፡፡
በሁለቱ ወራት ከሀገር ውስጥ የኃይል ሽያጭና ከፋይበር ኦፕቲክስ ኪራይ ከ2 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል መረጃ ያመለክታል።