የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አካባቢን የኤሌክትሪክ ችግር ለመፍታት መቸገሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ኃይል ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል
የላሊበላ እና የዋግ ኽምራ ዞን በርካታ አካባቢዎችም ለወራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አይደለም
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አካባቢ ኤሌክትሪክ በአጭር ጊዜ እንዲያገኝ ለማድረግ መቸገሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አሸብር ባልቻ እንደገለፁት በህወሓት ምክንያት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ኃይል ከተቋረጠ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።
የላሊበላ እና የዋግ ኽምራ ዞን በርካታ አካባቢዎችም ለወራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያገኙ አይደለም ማታቸውንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
እንደ አቶ አሸብር ገለፃ የላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ እና ሰቲት ሑመራ አካባቢዎች ኃይል ያገኙ የነበሩት በህወሓት ቡድን በተያዙ አካባቢዎች ከሚገኙ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከተዘረጉ መሥመሮች ነበር።
በዚህ የተነሳ የተቋረጡትን መሥመሮች ለመጠገንና አካባቢዎቹ ኃይል እንዲያገኙ ለማድረግ ተቋሙ መቸገሩን ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውቀዋል።
ለላሊበላና አካባቢው ሌሎች አማራጮችን እየታዩ በመሆናቸው በአጭር ጊዜ ሊፈቱ እንደሚችሉ የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ለወልቃይት ጠገዴ አካባቢ መፍትሔ ለመስጠት ከጎንደር ወይም ከመተማ ኃይል መዘርጋት ግድ ስለሚል ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።
በወልቃይት ጠገዴን ያለው ችግር ከሌሎች አካባቢዎች በተለየ ከዓመት በላይ የቆየው በአካባቢው አማራጭ መስመር ባለመኖሩና የአዲስ መስመር ዝርጋታው ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ይሁንና በአጭር ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት የክልሉ መንግስት፣ የፌደራል መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊሳተፉበት እንደሚገባ አቶ አሸብር ጠቁመዋል።
የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ኦፍ ግሪድ የሆኑ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነ አሳስበዋል።
ላሊበላን በጄኔሬተር መብራት ለመስጠት የተደረገው ሙከራ በነዳጅ አቅርቦት ምክንያት መስተጓጎሉ አይዘነጋም።