ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ለኬንያ ለመሸጥ የሚያስችልና 25 ዓመታት የሚቆይ ውል ማሰሯን ገለጸች
የኤሌክትሪክ ኃይል መጠኑ በሶስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚሸጥ ነው ተብሏል
አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሰዓት በ6 ነጥብ 5 የአሜሪካ ሳንቲም እንደሚቀርብ ተገልጿል
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ለኬንያ ለመሸጥ የሚያስችልና 25 ዓመታት የሚቆይ ውል ማሰሯን ገለጸች።
ውሉ ከህዳር 2015 ዓ.ም ጀምሮ የሚተገበር ነው ያለው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ የኃይል መጠኑ በሶስት ምዕራፎች የሚሸጥ ነው ብሏል።
የተቋሙ የማርኬቲንግ እና ቢዝነስ ልማት መምሪያ ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ህይወት እሸቱ እንደገለፁት ከመጪው ህዳር ጀምሮ ለሚቀጥሉት ተከታታይ ሶስት ዓመታት የኃይል ጭነት በማይበዛበት (Off-peak hours) የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጩ 65 ሜጋ ዋት እንዲሁም የኃይል ጭነት ከፍ በሚልበት ሰዓት (Peak hours) 200 ሜጋ ዋት እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደርሷል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ይቀርባል ያሉት አቶ ህይወት በስምምነቱ መሠረት የኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓት 150 ሜጋ ዋት እንዲሁም የኃይል ጭነት ከፍ በሚልበት ሰዓት 400 ሜጋ ዋት ለሽያጭ እንደሚቀርብ ገልፀዋል።
በሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ውሉ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በሁሉም ሰዓታት 400 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለኬንያ ለማቅረብ ስምምነት ላይ ተደርሷል ማለታቸውንም ከተቋሙ የማህበራዊ ገጽ ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።
አቶ ህይወት አንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሰዓት በ6 ነጥብ 5 የአሜሪካ ሳንቲም እንደሚቀርብ የገለፁ ሲሆን ከአምስት ዓመታት በኃላ በተቋሙ ጠያቂነት አሁን በተደረሰው የታሪፍ ዋጋ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ድርድር እንደሚኖር ጨምረው አብራርተዋል።
እንደ ተወካይ ዳይሬክተሩ ገለጻ ኬንያ የታሪፍ ቅናሽ ጥያቄ ማቅረቧን እና ከአስር ዓመት በፊት ስምምነት ላይ ተደርሶበት የነበረው 400 ሜጋ ዋት ላይ መጠኑ እንዲቀነስላት መጠየቋን ተከትሎ ፕሮጀክቱ በታሰበው ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሳይሆን ቀርቷል። ይህም ድርድሩ እንዲዘገይ ማድረጉንም ነው አቶ ህይወት የገለጹት።
የሁለቱ ሃገራት የኃይል ሽያጭ ስምምነት መጠናቀቁን ተከትሎ ባሁኑ ሰዓት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን የመፈተሽ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ህዳር ወር መጀመሪያ ላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጩ በይፋ እንደሚጀመርም ተናግረዋል።
የኢትዮ - ኬንያ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ለማቅረብ ላቀደችው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሔደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ ይታወሳል።