በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በአዋሽ ፈንታሌ 15 ሺህ ሰዎች ለአደጋ ተጋላጭ መሆናቸው ተገለፀ
በተመሳሳይ በዱለቻ ወረዳ በ2 ቀበሌዎች 20 ሺህ ሰዎች በአደጋ ስጋት ውስጥ እንደሚኖሩ ተገልጿል
ኮሚሽኑ በአፋር እና በኦሮሚያ እየተከሰተ ባለው የርዕደ- መሬት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን ወደሌሎች አካባቢዎች የማስፈር ስራ እየሰራሁ ነው ብሏል
በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተከሰተ ባለው ርዕደ መሬት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ወደሌሎች አካባቢዎች የማስፈር ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ እንዲሁም በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች አዋሽ ፈንታሌና ዱለቻ (ዱለሳ) ወረዳዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለችግሩ ተጋላጭ ናቸው ብሏል፡፡
በሁለቱም ወረዳዎች በአዋሽ ፈንታሌ 6 ተጋላጭ ቀበሌዎች 15 ሺህ ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ÷ እስከ አሁን 7 ሺህ ወገኖች ከስጋቱ ቀጣና ወደ ሌላ ስፈራ መጓጓዛቸው ተመላክቷል፡፡
በዱለቻ ወረዳ ደግሞ በ2 ቀበሌዎች የሚገኙ 20 ሺህ የሚሆኑ ወገኖች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ ከነዚህ ቀበሌዎች እስከ አሁን 6 ሺህ 223 ነዋሪዎች አካባቢውን መልቀቃቸውን ነው መግለጫው የጠቀሰው፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ በ5 ቀበሌዎች 16 ሺህ 182 ነዋሪዎች ተጋላጭ መሆናቸው ሲገለጽ ከነዚህ መካከል 7 ሺህ 350 ነዋሪዎች ከተጋላጭ ስፍራ ወጥተዋል፡፡
8 ሺህ 832 የሚሆኑት ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ከስፍራው እንዲንቀሳቀሱ እየተሠራ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ከስተቱን ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲና ከሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት በተውጣጡ የሳይንቲፊክ ኮሚቴ አባላት አማካኝነት እየተከታተልኩ ነው ያለው ኮሚሽኑ ፤መገለጽ ያለባቸውን ቅድመ ጥንቃቄዎች አስመልከቶ አስፈላጊው መረጃ ለሕዝብ በተከታታይ እንደሚያቀርብ ገልጿል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን በተመለከተ እስከ አሁን 70 ሺህ ለሚጠጉ የሀብረተሰብ ክፍሎች የሚሆን 11,550 ኩንታል ምግብ-ነክ እና ለ7ሺ አባወራ የሚሆን ምግብ-ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ስፍራው ተልኳል ነው የተባለው፡፡
ለምግብ እና ምግብ-ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ሁለት መቶ ሰማኒያ አንድ ሚሊየን አምስት መቶ ስልሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር እንደሚገመት ታውቋል፡፡