ኢትዮጵያ አልሸባብን ለመከላከል ሶማሊያ ውስጥ "በፈር ዞን" በማዘጋጀት ወታደሮቿን የማሰማራት መብት አላት-አምባሳደር ተፈራ
አምባሳደሩ አልሸባብ ለኢትዮጵያ ስጋት በመሆኑ ኢትዮጵያ ባለበት አካባቢ እንቅሰቃሴውን ብትከታተል ይመረጣል ብለዋል
ሶማሊሊንድ ከሶማሊያ የተሻለ የመንግስትነት ቁመና ላይ ትገኛለች ሲሉ አምባሳደሩ አነጻጽረዋል
ባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ አመት መጀመርያ በኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ መካከል የወደብ የመግባብያ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በአዲስአበባ እና ሞቃዲሾ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተፈጥሯል፡፡
ስምምነቱ “ሉአላዊነቴን ጥሷል” ያለቸው ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገር ከማስወጣት ጀምሮ ከአዲስ አበባ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከሚገኙ የቀጠናው ሀገራት ጋር ወዳጅነቷን እያጠበቀች ነው፡፡
በነሀሴ ወር ደግሞ ሶማሊያ እና ግብጽ የወታደራዊ የትብብር ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በመጪው ጥር ወር የስራ ጊዜው የሚጠናቀቀውን (አትሚስ) የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) ውስጥ ካይሮ እስከ 5 ሺ የሚደርሱ ወታደሮቿን ለማሰማራት እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡
ግብፅ በሶማሊያ ያላትን ወታደራዊ ሚና የምትነቅፈው ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በጥር ወር የገባችውን ስምምነት የቀይ ባህር መዳረሻ የባህር ትራንስፖርትን ለመጠበቅ እና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ያስችላል ስትል ስትከራከር ቆይታለች።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ደግሞ የሶማሊያ መከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር መሀመድ ኑር "እስካሁን በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የማትሳተፍ ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ማረጋገጥ እችላለሁ” ብለዋል።
ሶማሊያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮው ውስጥ የሚሳተፉ ሀገራትን የመምረጥ መብት እንዳላት የሚናገሩት የሶማሊያ ባለስልጣናት የወደብ ስምምነቱ ካልተሰረዘ ኢትዮጵያ በተልዕኮው ውስጥ እንደማትሳተፍ በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ በአዲሱ የሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ልዑክ ውስጥ አለመሳተፏ እና የግብጽ እና ሶማሊያ ወታደራዊ ትብብር ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዲሁም ቀጣናዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አል ዐይን አማርኛ ከቀድሞ የምስራቅ አፍሪካ ጦር ሀላፊ እና ዲፕሎማት አምባሳደር ተፈራ ሻወል ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
አል ዐይን አማርኛ፡- እስኪ ወቅታዊ የምስራቅ አፍሪካ ሁኔታ በተመለከተ ?ከታዘቡት እንጀምር
አምባሳደር ተፈራ ፡- የአፍሪካ ቀንድ አንተም እንደምታውቀው እጅግ ተቀያያሪ ፖለቲካ የሚስተዋልበት በቀጠናው የሚኖሩ ሀገራት አብዛኞቹ ያልተረጋጋ ፖለቲካ ያላቸው እና ሽብርተኞች የሚንቀሳቀሱበት ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ስፍራው ለቀይ ባህር ካለው ቅርበት እና ከሌሎች ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሀያላን ሀገሮችን ጨምሮ አቅማቸው እየፈረጠመ የመጡት የአረብ ሀገራት ጭምር ፍላጎት የሚያንጸባርቁበት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህ የተነሳ በአካባቢው አንድ ሀገር ከራሱ ድንበር ክልል ውጪ ተሻግሮ የሚያሳልፈው ውሳኔ በቀጠናው ውጪ ያሉትን ሀገራት ጭምር የሚነካ ነው እና በቀላሉ ፍላጎትን ማስፈጸም አስቸጋሪ ነው፡፡
ከዚህ ባለፈ ሀገራቱ በኢኮኖሚ እምባዛም ያልተደራጁ በመሆናቸው እንዲሁም የሰላም እና ጸጥታ ፣የፖለቲካ ሁኔታቸውም ጠንካራ ባለመሆናቸው ቀጠናው ውስጥ የሚፈጠር ችግር ለመቀጣጠል ፈጣን ሲሆን ለመብረድ ግን ጊዜ ይፈጅበታል፡፡
አሁን የሚታየው ውጥረት መነሻውም አካባቢው የብዙ ሀገራት ፍላጎት ስላለበት አንዱ የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚሄድበት ርቀት ሌሎች ተቀናቃኞች የዚህ ተቃራኒ ሆነው ለመቆም በሚፈጥሩት ገመድ ጉተታ የሚከሰት ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ፡- ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ከፈጸመች ጀምሮ የአካባቢው ውጥረት ከፍ እንዳለ ይነገራል፤ እርሶ የኢትዮጵያን የወደብ ጥያቄ እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደር ተፈራ ፡- ማንም ሀገር የመልማት እና የብሔራዊ ደህንንቱን የማስጠበቅ መብት አለው፡፡
ይህን ስታደርግ ከአንተ ጋር የሌለውን ከሌሎች ማማተርህ አይቀርም፤ ዲፕሎማሲ እና ሰጥቶ መቀበል መርህ የሚለው አሰራር የሚተገበረው እዚህ ላይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየጊዜው የህዝቧ ቁጥር እና የኢኮኖሚያዋ ሁኔታ እያደገ ያለች ሀገር ናት። ከዚህ አንጻር ራሴ የማስተዳድረው ወደብ ይኑረኝ ብላ መነሳቷ ተገቢ እና ትክክለኛ ጥያቄ ነው ብየ አምናለሁ፡፡
እኔ እንደውም ይሄ ሁሉ አለምአቀፋዊ ቀውስ እና ብጥብጥ ባለበት በዋነኛነት በአንድ ወደብ እስካሁን መዝለቃችን ያስገርመኛል፡፡
ከሶማሊላንድ ጋር የተፈጸመው የወደብ ስምምነት በዚህ ልክ ለምን እንዳነጋገረ አይገባኝም ፤ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሀገር ጋር ስምምነት ለመፈጸም የመጀመርያዋ ሀገር አይደለችም። የሶማሊያም ጩኸት ለምን በዚህ ልክ እንደተጋነነም አላውቅም፡፡
ከዚህ ቀደምም አረብ ኤሜሬትስ የወደብ ኩባንያ ዲፒ ወርልድ የበርበራን ወደብ አልምቶ ለመጠቀም ተስማምቷል። በይፋ አይነገር እነጂ ሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ እና የምዕራባውያን ሀገራት በተመሳሳይ ከሶማሊላንድ ወደብ መከራየት ፍላጎት እንዳለቸው የቢዝነስ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነትም እንደሚያካሄዱ ግልጽ ነው፡፡
ኢትዮጵያም ልክ እንደሌሎቹ ሁሉ ነው ወደብ ለመከራየት ጥያቄ ያቀረበችው፡፡ ስለዚህ ለጠየከኝ ጥያቄ የኢትዮጵያ የወደብ ስምምነት ትክክለኛ ጥያቄ ነው፤ ጥቅሙ ደግሞ ከእኛ አልፎ ሶማሊያንም ሶማሊላንድንም የሚጠቅም ፣ በቀጠናው ያሉ የጸጥታ ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችል ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በተደጋጋሚ ሶማሊያ ስምምነቱ ሉአላዊነቴን የሚጥስ ነው በሚል የምታነሳውን ጥያቄ እንዴት ይመለከቱታል?
አምባሳደር ተፈራ፡- ሶማሊላንድ ሀገር መሆኑን ከማወጁ በፊት በእንግሊዝ የሚተዳደር ነበር፤ ሶማሊያን ደግሞ ጣሊያን በቅኝ ግዛት ይዟታል። ከቅኝ ግዛት ማብቃት በኋላም ለቀናት ራሱን የቻለ መንግስት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከዛ ከሶማሊያ ጋር ለመወሀድ ከወሰነ በኋላ በዚያድ ባሬ መንግስት ብዙ በደል ደርሶበታል የዚያድ ባሬን መንግስት መውደቅ ተከትሎ እራሱን የቻለ ሀገር ለመሆን አወጀ፡፡
እንግዲህ ከዚህ ጊዜ በኋላ በሞቃዲሾ እና በሀርጌሳ በኩል ያለውን ልዩነት ብትመለከት ፍጹም የማይገኛኙ ናቸው፤ በሰላም ሁኔታ ፣ በኢኮኖሚ ፣ በወታደራዊ አቅም ፣ በፖለቲካ እና በሌሎችም መመዘኛዎች ብትመለከት ሶማሊላንድ ከሶማሊያ የተሻለ የሀገርነት ቁመና ያለው ነው፡፡
እና እንዴት ነው የዋና ከተማውን ሰላም ራሱን ችሎ ማስጠበቅ ከማይችል ሀገር ጋር መጥተህ ተዋሀድ የምትለው፤ ይሄ በፍጹም የሚሆን ነገር አይደለም። የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሀርጌሳ ሀገር ሆና ልትመሰረት እንደምትችል እምነት አለኝ፡፡
የሶማሊያ መንግሰትም አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ከ10 አመት በላይ በውጭ ሀገራት ወታደሮች ድጋፍ እየተዳደረ ከእርሱ በተሻለ ሁኔታ ላይ የምትገኝውን ሶማሊላንድ የግዛት አካሌ ነች በሚል ሉአላዊነቴ ተደፈረ ብሎ መነሳት ምክንያታዊ መስሎ አይሰማኝም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም ማስከበር እና ደህንነት የከፈለችው መስዕዋትነት እንዴት ይታያል?
አምባሳደር ተፈራ ፡- በፈረንጆቹ 2014 በሶማሊያ የሰላም አስከባሪ ልዑክ አሚሶም ሲቋቋም ከኡጋንዳ ቀጥሎ አስቀድመው ወደ ስፍራው ጦራቸውን ከላኩ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡
10 አመታት እና ከዛ በላይ በሆኑ ጊዜያት ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ መንግስት ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ እና በአሁኑ መንግስትም ለሶማሊያ ሰላም ያልተቋረጠ ድጋፍ አድርገናል፡፡
የኢትዮጵያ ሰራዊት በልዑኩ ውስጥ ከሚሳተፉ ሀገራት ወታደሮች በተለየ በስነምግባር ፣ በጀግንነቱ እና በአመራር ጥበቡ የሚታወቅ ነው፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ወታደሮችንም ህይወት በሶማሊያ እንደተሰው ማንም የሚያውቀው ነው፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ስታደርግ የአልሸባብ መጠንከር ለእኔም ስጋት ነው ከሚል እሳቤ የመነጨ ብቻ አልነበረም ፤ ጎረቤታዊ አጋርነት እና በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ የመቆም መርህን ታሳቢ በማድረግ ነበር፡፡
ይህንን የቀደሙቱም አሁን ያሉትም መሪዎች ህዛባቸውም ጭምር የሚያውቀው ሀቅ ነው፤ ዛሬ ላይ ልዩነት ተፈጠረ ተብሎ ከኢትዮጰያ ጥቅም ጋር ተጻራሪ ቆመዋል ተብለው ከሚታሰቡ ሀገራት ጋር ሂዶ መወዳጀት ከመበሻሻቅ ያለፈ ጥቅም አይኖረውም፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በአሁኑ ወቅት ሞቃዲሾ ከካይሮ ጋር የመከላከያ እና ደህንነት ስምምነት ፈጽማለች ከዚህ በተጨማሪም ግብጽ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ እና በሁለትዮሽ ስምምነት 10 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን በስፍራው ለማስመራት አቅዳለች ይህ በኢትዮጵያ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?
አምባሳደር ተፈራ፡- እኔ እውነቱን ንገረኝ ካልክ ይሄ ብዙም አያስጨንቀኝም እንደውም ከሚገባው በላይ ተጋኗል ብየ አስባለሁ፡፡
ግብጾች አይደለም ሶማሊያ ውስጥ ቢችሉ እዚህ ሀገር ገብተው የመንግስትን እንቅስቃሴ ቢቃኙ ቢከታተሉ ደስታቸው ነው፡፡
ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ከአስርተ አመታት በላይ እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ከሰሱ እርሱም አልተሳካም። ግድቡ አሁን ተጠናቆ የአባይ አጀንዳ ወደመዘጋቱ እየተቃረበ ይገኛል፡፡
በታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር በተገናኝ ካላቸው የሄጂሞኒ ወይም የበላይነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የትኛውንም ኢትዮጵያን የሚጎዳ ወይም ጉዞዋን የሚያሰናክል አጋጣሚ ካገኙ ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም ይህን ግልጽ አድርጌ ልነግርህ እፈልጋለሁ፡፡
አሁን እያየን ያለው የሞቃዲሾ ተቆርቋሪ እና ወዳጅ ሆኖ የመቅረብ አዝማሚያ፣ ሶማሊያ ከተነካች ግብጽ ዝም ብላ አትቀመጥም ፉከራ የመጣውም ከዚሁ ነው፡፡
በእርግጥ ለሀገሪቱ ሰላም ደህንነት እና ሉአላዊነት የሚጨነቁ ከሆነ የዛሬ አስር አመት የት ነበሩ?፤ ሶማሊያ በአልሸባብ ቦምብ ስትጋይ ፣ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ሲሞቱ ለምን እናግዛችሁ ብለው አልመጡም ? ፤ወይስ አልሸባብ እና የሶማሊያ ችግር የመጣው ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነው?
አየህ እነኚህን ጥያቄዎች ተዘዋውረህ ስትመለከት ይህ ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም በምትከተለው ፖሊስ ሶማሊያን ለመጠቀም በማሰብ ብቻ ወዳጅ መስላ እንደቀረበች ይገባሀል፡
ስለዚህ ከዚህ በፊትም ያረጉት ነው ፣ ዛሬም እያደረጉት ነው ፣ ወደፊትም የሚያደርጉት ይሆናል፡፡ በዚህ የተነሳ አደጋን የሚፈጥር አንዳች ነገር ቢከሰት የኢትዮጵያ መንግሰት ይህን በተገቢው መንገድ ይረዳል ብየ ስለማስብ ተመጣጣኝ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ መልስ ለመስጠት የራሱ ዝግጁነት እንደሚኖረው እገምታለሁ፡፡
ጎን ለጎን ግብጽ ወደ ቀጠናው መጠጋቷ የሚፈጥረውን ቀውስ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለአፍሪካ ህብረት በማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን በሰፊው መጠቀም ይጠይቃል፡፡
የሶማሊያ መሪዎች ነገሮችን ልብ ማለት ቢችሉ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን አስቀድማ ወዳጅ ሆና የቆመች ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች ይገባቸው ነበር፤ ግብጾቹ ነገ ኢትዮጵያን የሚያሰናክሉበት ሌላ የተሻለ አማራጭ ካገኙ እመነኝ ከሞቃዲሾ ነቅለው ነው የሚወጡት በዚህ መሀል የምትጎዳው ሶማሊያ ነች፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ጥር ወር በሚጀምረው አዲሱ በሶማሊያ የአፍሪካ ሀብረት ተልዕኮ ውስጥ ኢትዮጵያ አለመካተቷ የሚያስከትለው ተጽእኖ ይኖር ይሆን?
አምባሳደር ተፈራ፡- አልሸባብ ለኢትዮጵም ስጋት ነው ይህ የሚካድ አይደለም፤ ቡድኑ እንዳያንሰራራ እዛው በሚገኝበት አካባቢ እንቅስቃሴውን እያጠናን መከላከል ብንችል ይመረጣል ወይ? ለእርሱም አዎ ነው መልሴ፡፡
በእርግጥ አትሚስ የሚባለው ልኡክ በ2025 ሙሉ ለሙሉ የሰላም ማስከበር ስራውን ለሀገሪቱ ጸጥታ ሀይሎች አስረክቦ ለመውጣት እቅድ ነበረው በሶማሊያ መንግስት ጥያቄ ነው ተልዕኮው የተራዘመው፤ አዲስ የሚገባው ልኡክም እስከ 2028 ለሶስት አመታት ብቻ ነው የሚቆየው፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ በአካባቢው የደህንነት ስጋት ስላለባት ሁኔታዎችን በቅርበት ለመከታተል ያላትን ፍላጎት ከማሳጣቱ ባለፈ እምብዛም እንድምታ ይኖረዋል ብየ አላምንም፡፡
ነገር ግን አንድ ሀገር የሰላም አስከባሪ ወታደር እንዲሰማራ ስትጠይቅ የተሳታፊዎቹን ሀገራት የመምረጥ መብት ሙሉ መብት አላት፡፡
ያ ማለት ግን ሶማሊያ አልፈለገችም ተብሎ ደግሞ እጅህን አጣጥፈህ ትቀመጣለህ ማለት አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አስርተ አመታት አልሸባብን ለመዋጋት የነበራትን ሚና አስተዋጽኦ አንዲሁም ተልዕኮውን በማስተባበር እና በመምራት የነበራት ልምድ እንዲሁ የሚተካ አለመሆኑን የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በገንዘብ እና በተለያየ ሁኔታ ለሚደግፉ እንደ አውሮፓ ህበረት ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለኢጋድ እና ለአፍሪካ ህብረት አቤት ማለት አለባት፤ አቋሟን በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ቻናሎችን በመጠቀም ተጽዕኖ ለመፍጠር መንቀሳቀስ ይኖርባታል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ኢትዮጵያ በተልዕኮው ውስጥ አለመሳተፏ ከተረጋገጠ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እና ደህንነቷን ለማስጠበቅ ምን ማደረግ ይኖርባታል?
አምባሳደር ተፈራ፡- ይሄ እንግዲህ በቅድሚያ የውስጥ ሰላምን ከማስጠበቅ ይጀምራል ኢትዮጵያ ከግብጽም ሆነ ከሌሎች ተቀናቀኞቿ ትንኮሳ የሚደርስባት የውስጥ ሰላሟ ችግር ውስጥ በገባ ጊዜ ነው፡፡
የአፍሪካ ቀነድ አሁን የጋዛው እና የዩክሬኑ ጦርነት ካለቀ የአለም አቀፍ ትኩረት ማዕከል ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፤ ስለዚህ በውስጥ ለመባላት እና ለመጋጨት የምናባክነው ጊዜ ሊኖር አይገባም፡፡
በአለም አቀፍ መድረክ ብሔራዊ ጥቅምህን ለማስጠበቅ ተገዳዳሪ ሆነህ ለመቅረብ ውስጣዊ አንድነትህን እና ሰላምን ማጠናከር ይኖርብሀል፤ በመሆኑም የውስጥ ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡
ቀጥሎ ግብጽ እና ሶማሊያ አሁን ባለው ልክ ግንኙነታቸውን እያሰደጉ ከመጡ እኛም ወዳጅ ከምንላቸው ሀገራት ጋር የመከላከያ እና የደህንነት ስምምነት መፈጸም ይኖርብናል፡፡
አልሸባብ እና በአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ውስጥ አለመሳተፋችንን በተመለከተ ደግሞ አንድ ሀገር በሌላ ሀገር ውስጥ የሚገኝ ግጭት እና ብጥብጥ ወይም ሽብርተኝነት ስጋት ይሆንብኛል ካለ ከድንበር ጠጋ ብሎ “በፈር ዞን" (ኮጦር ነጻ ቀጣና) በማዘጋጀት ወታደሮቹን አሰማርቶ ድንበሩን የማስጠበቅ መብት አለው፡፡
ከሁሉም በፊት ግን ዲፕሎማሲ ትልቅ አቅም ያለው መሳርያ በመሆኑ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ እና በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነት በመጠቀም እውነታዎቿን ለማስረዳት እና ጥቅሟን ለማስከበር ጠንከር ያለ የዲፕሎማሲ ልዑክ በማሰናዳት ዘመቻ ብታደርግ መልካም ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- እናመሰግናለን።
አምባሳደር ተፈራ፡- እኔም አመስግናለሁ።