አሜሪካ ኢራቅን በወረረችበት ወቅት ግፍ ለተፈጸመባቸው ዜጎች 42 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ተወሰነ
በአሜሪካ ጦር የተቀጠረ አንድ ኩባንያ በሶስት ኢራቃዊን ላይ ማሰቃየትን ፈጽሟል ተብሏል
ግለሰቦቹ ለተፈጸመባቸው አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶች ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው ሲከራከሩ ቆይተዋል
አሜሪካ ኢራቅን በወረረችበት ወቅት ግፍ ለተፈጸመባቸው ዜጎች 42 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ተወሰነ፡፡
አሜሪካ ከ20 ዓመት በፊት በሳዳም ሁሴን የሚመራውን የኢራቅ አስተዳድር ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ ታጥቋል በሚል ጦሯን ወደ ባግዳድ መላኳ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካ እና አጋሮቿ ጦር የሳዳም ሁሴንን አስተዳድር በሀይል በማፍረስ አዲስ አስተዳድር የተመሰረተ ሲሆን በርካታ ዜጎችም ለስቃይ እና እንግልት ተዳርገዋል ተብሏል፡፡
የዚህ አካል የሆነ እና በአሜሪካ ጦር የተቀጠረ ካሲ ፕሪሚየር ቴክኖሎጂ የተሰኘ የአሜሪካ ስራ ተቋራጭ ድርጅት በሶስት ኢራቃዊን ላይ ድብደባን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶችን አድርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ይህ ኩባንያ አቡ ጋሪብ በተሰኘ ቦታ የተለያዩ ማሰቃያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ በኢራቃዊያኑ ላይ ጥቃት አድርሷል የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡
ለዓመታት በቀጠለው በዚህ ክስ የቨርጅኒያ ፍርድ ቤት ኩባንያው በተከሰሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ኩባንያው ለከሳሾች 42 ሚሊዮን ዶላር የጉዳት ካሳ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
ለ10 አመታት በስህተት የታሰረው አሜሪካዊ 50 ሚሊየን ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ተወሰነ
ኢራቃዊያኑ በወቅቱ ለቀናት እንቅልፍ እንዳይተኙ ማድረግ፣ ድብደባ እና ሌሎች ከባድ እንግልቶች እንደደረሱባቸው ተገልጿል፡፡
የትምህርት ቤት ዳይሬክተር፣ አትክልት ቸርቻሪ እና ጋዜጠኛ እንደሆኑ የተገለጹት ሶስቱ ኢራቃዊያን ለእያንዳንዳቸው 14 ሚሊዮን ዶላር የጉዳት ካሳ እንዲከፈላቸው ተወስኖላቸዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ህገ መንግስታዊ መብት ማዕከል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ያደነቀ እና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ቅጣቱ የተላለፈበት ካሲ ኩባንያ በበኩሉ ውሳኔው የሚያበሳጭ መሆኑን ገልጾ ይግባኝ እንደሚል ገልጿል፡፡