በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ስር በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤት አስረዱ
አቃቢ ህግ በዚህ መዝገብ ስር ላሉ ተከሳሾች ወንጀሉን እንደፈጸሙ የሚያስረዱ 96 ምስክሮች እንዳሉት ገልጿል
ተከሳሾች ክሱ የተመሰረተብን አማራ በመሆናችን ነው ሲሉ ለፍርድ ቤት በሰጡት የእምነት ክህደት ላይ ተናግረዋል
በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ስር በሽብር ወንጀል የተከሰሱ ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ ለፍርድ ቤት አስረዱ፡፡
በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ መዝገብ ስር ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ዛሬ ልደታ በሚገኘው ፍርድ ቤት ችሎት ቀርበዋል፡፡
በዚህ መዝገብ ስር ክስ ከተመሰረተባቸው እና በማረሚያ ቤት ከሚገኙ 23 ተጠርጣሪዎች መካከል ዶክተር ወንደሰን አሰፋ፣ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው፣ መስከረም አበራ፣ ገነት አስማማው እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በዚህ መዝገብ ስር 51 ተጠርጣሪዎች የሽብር ወንጀል ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/12 ጥሰዋል በሚል የሽብር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአዋጁ አንቀጽ 3/2 ሀ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ክስ እንደደረሳቸው የተጠርጣሪዎች ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
አቃቢ ህግ ባሳለፍነው ሰኞ ያሻሻለውን ክስ ለተጠርጣሪዎች እንዲደርሳቸው ያደረገ ሲሆን የተከሳሾችን እምነት ክህደት ቃል ለመቀበል በወቅቱ ባለመሟላታቸው ለዛሬ ህዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሮ እንደነበር ጠበቃ ሰለሞን አክለዋል፡፡
ይህን ተከትሎም ክስ ከተመሰረተባቸው 51 ተጠርጣሪዎች መካከል 23ቱ በአካል ቀርበው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለፍርድ ቤት መስጠታቸው ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በዛሬ የችሎት ውሏቸው “የተመሰረተብንን የሽብር ወንጀል ክስ አልፈጸምንም፣ ክሱ የተመሰረተብን በማንነታቸው አማራ በመሆናችን እና የአማራ ህዝብ ከተቃጣበት ጥቃት ራሱን እንዲከላከል በማስተማራችን ነው፣ ይህን ማድረጋችን ደግሞ ወንጀል ሊሆን አይገባም” ብለው ለፍርድ ቤቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል ሲሉ ጠበቃ ሰለሞን ነግረውናል፡፡
አቃቢ ህግ በተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጥ ከፍርድ ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄ ተጠርጣሪዎች የሽብር ወንጀል መፈጸማቸውን የሚያስረዱ 96 ምስክሮች እንዳሉት ለፍርድ ቤቱ መናገሩም ተገልጿል፡፡
ተከሳሾችም አቃቢ ህግ አሉኝ ያላቸውን የምስክሮች ዝርዝር ለፍርድ ቤት ያቅርብልን ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል ያሉት ጠበቃ ሰለሞን ፍርድ ቤቱም አቃቢ ህግ የምስክሮችን ዝርዝር እንዲያቀርብ አዟል ተብሏል፡፡
ፍርድ ቤቱም የአቃቢ ህግ 96 ምስክሮችን ቃል ለመቀበልም ከታህሳስ 7 እስከ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን ከጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ሰምተናል፡፡
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን ወንጀል አዋጅ ቁጥር 1176/12 አንቀጽ 3/2 ሀ ላይ በመተላለፍ የሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡
ከ19 ወራት በፊት የፌደራል መንግስት “የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ” የሚል ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጽታ ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተጀመረው ጦርነት እንደቀጠለ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ከአንድ ዓመት በላይ በእስር ላይ ሲሆኑ የተከሰሱበት መዝገብም እልባት አላገኘም፡፡