ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን የነጻነት ቀን በዓል አከባባር ጎን ለጎን ችግኝ እንዲተከል ያላትን ፍላጎት ገለጸች
የግብጽ የመስኖና ውሃ ሃብት ሚኒስትር መሃመድ አብደል አቲ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጁባ መግባታቸው የሚታወስ ነው
“ኢትዮጵያውያን ለደቡብ ሱዳን ነጻነት እስከ ሕይወት መስዕዋትነት የደረሰ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል”- ምክትል ፕሬዝዳንት ጄምስ ዋኒ
ኢትዮጵያ በመጪው ሃምሌ 2 ከሚከበረው የደቡብ ሱዳን 10ኛ ዓመት የነጻነት ቀን በዓል አከባባር ጎን ለጎን ችግኝ እንዲተከል ያላትን ፍላጎት ገለጸች፡፡
በጁባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነቢል ማህዲ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንትጄምስ ዋኒ ኢጋ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ሁለቱን አገራት በመንገድና በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት እንዲሳካ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ነቢል ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብርን በጎረቤት አገራት ጭምር ለማስጀመር የያዘችውን ዕቅድ ለምክትል ፕሬዝዳንቱ ገልጸውላቸዋል።
በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 7 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ያቀደችው ኢትዮጵያ 1 ቢሊየን ችግኞችን ለጎረቤት ሀገራት እንደምትሰጥ ቀደም ሲል ማስታወቋ የሚታወስ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ደቡብ ሱዳን በቅርቡ ለ10ኛ ጊዜ ከምታከብረው የነጻነት ቀኗ አከባባር ጎን ለጎን ችግኝ ተከላው አንድ አካል እንዲሆን ፍላጎት መኖሩን ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዝዳንቱም ዕቅዱ በጣም ጠቃሚና ወቅታዊ መሆኑን በመግለጽ ለተግባራዊነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
በስተምስራቅ ከኢትዮጵያ ጋር የምትዋሰነውና ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ተገንጥላ በ2003 ዓ/ም ነጻነቷን ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
ለዚህ ስኬትም ኢትዮጵያውያን እስከ ሕይወት መስዕዋትነት የደረሰ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል እንደ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄምስ ዋኒ ገለጻ፡፡
አምባሳደር ነቢል በሕዳሴ ግድብ ድርድር ሂደት፣ በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ እንዲሁም የምርጫውን በሰላም መጠናቀቅ አስመልክተው ገለጻ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በውሃ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር እመክራለሁ በሚል የግብጽ የመስኖና ውሃ ሃብት ሚኒስትር መሃመድ አብደል አቲ እስከፊታችን አርብ ለሚዘልቅ ጉብኝት ከትናንት በስቲያ ሰኞ ጁባ መግባታቸው አይዘነጋም፡፡