ፓርላማው የተበተነው በ2018 በተደረገው ስምምነት መሰረት ተቃዋሚዎች የተካተቱበት አዲስ ፓርላማ ለማዋቀር ነው
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት የሀገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት (ፓርላማ) እና የክልል ምክር ቤቶች እንዲበተኑ ወስነዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ውሳኔውን ያሳለፉት እ.ኤ.አ. በ2018 በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ፣ የሀገሪቱ መንግስት ተቃዋሚዎች የተካተቱበት አዲስ ፓርላማ እንደገና እንዲዋቀር ለማድረግ ነው፡፡
የሀገሪቱ የሽግግር ም/ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች እንዲበተኑ የሚደነግገው የፕሬዝደንቱ ውሳኔ የተነገረው ቅዳሜ ምሽት ላይ በመንግስት ቴሌቪዥን በተላለፈው ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ ነው፡፡
በመንግስት ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ በይፋ ከጁባ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የብሔራዊው ፓርላማ አባላት እና የክልሎች ምክር ቤት አባላት የአገልግሎት ጊዜ አብቅቷል፡፡
በ2018ቱ የሰላም ስምምነት የተሳተፉ ፓርቲዎች 400 አባላት የነበሩት ብሔራዊ ፓርላማው 550 አባላትን እንዲያካትት የተስማሙ ሲሆን በሳልቫ ኪር የሚመራው መንግስት 332 አባላት ሲኖሩት ፣ በሪክ ማቻር የሚመራው የታጠቀ የተቃዋሚ ቡድን ደግሞ 128 አባላት ይኖሩታል፡፡ ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በ 90 አባላት ይወከላሉ፡፡
ፓርቲዎቹ በተጨማሪም የክልሎች ምክር ቤቶች በሰላም ስምምነቱ ለእያንዳንዱ ፓርቲ በተመደበው መጠን የሚከፋፈሉ 100 አባላትን እንዲያካትቱም ተስማምተዋል፡፡ እስካሁን የክልል ም/ቤት አባላት 50 የነበሩ ሲሆን በአዲሱ ስምምነት መሠረት የአባላቱ ቁጥር በእጥፍ አድጓል፡፡
የመንግስት የስራ አስፈፃሚ አካል ባለፈው ዓመት መመስረቱን ተከትሎ ሁለቱ ምክር ቤቶች ተበትነው እንደአዲስ መዋቀር የነበረባቸው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር፡፡
ይህ በመዘግየቱ ምክንያት ታዛቢዎች እና አንዳንድ የመንግስት ባለሥልጣናት ሁለቱን ተቋማት ህጋዊ አልነበሩም በማለት ዕውቅና ነፍገው ቆይተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በስምምነቱ መሠረት ህጎችን እና ማሻሻያዎችን ለማውጣት አስቸጋሪ አድርጎ ስለመቆየቱ ይገለጻል፡፡ ምዕራባውያን ሀገራትም በደቡብ ሱዳን ላይ ጫና ሲያሳድሩ ነበር፡፡
የሀገሪቱ ፕሬዝደንት በቀጣዩ ሳምንት አዲሱን ፓርላማ ያቋቁማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡