ፖለቲካ
በደቡብ ሱዳን ዳግም ግጭት ሊያገረሽ ይችላል- ተመድ
በፕሬዚዳንት ሳለቫ ኪር እና በተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል አልፎ አልፎ ግጭቶች ይስተዋላሉ
በሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች ላይ የአዲስ የጦር መሳሪያ ግዢ ማእቀብ ሊጣል ይገባል- ተመድ
በደቡብ ሱዳን ዳግም ግጭጽ ሊያገረሽ ይችላል ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስጋቱን ገልጿል።
የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች የደረሱት የሰላም ስምምነት አፈጻጸም መጓተት ሀገሪቱን ዳግም ወደ ከፍተኛ ግጭት ሊያስገባ እንደሚችል ድርጅቱ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሀይሎች የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ 3 ዓመት ሞልቷል ያለው ተመድ፤ ሆኖም ግን በፕሬዚዳንት ሳለቫ ኪር እና በተቃዋሚ መወሪው ሪክ ማቻር ደጋፊዎች መካከል አልፎ አልፎ ግጭቶች እንደሚስተዋሉም ገልጿል።
ደጋፊዎች መካከል የሚስተዋሉት ግጭቶች ለደቡብ ሱዳን ዜጎች አስፈላጊ የሆኑ የሰብአዊ ድጋፎች እንዳደርሱ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህም የሀገሪቱን ዜጎች ለከፋ ጉዳት እየዳረገ መሆኑን አስታውቋል።
አዲሱ የመንግስታቱ ድርጅጽ ሪፖርት አክሎም የሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚ እንዳይሆን እንቅፋት በሚሆኑ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሀይሎች ላይ የአዲስ የጦር መሳሪያ ግዢ ማእቀብ እንዲጣል እና ከዚህ በፊት የተጣሉ ማእቀቦችም እንዲራዘሙ ጠይቋል።