ተመድ በትግራይ ላሉ ኤርትራውያን ስደተኞች የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ አልቻልኩም አለ
የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፤ በዳባትአለምዋጭ ለሚገኙ ስደተኞችን መሰረታዊ የሰብአዊ እርዳታ እየሰጠ መሆኑ ገልጿል
በትግራይ ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 10 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ችግር ላይ እንደሚገኙም ተመድ አስታውቋል
በትግራይ ለሚገኙት ኤርትራውያን ስደተኞች ይሰጥ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ መቋረጡ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን /ዩኤንኤችሲአር/ ጽ/ቤት ለአል-ዐይን አማርኛ በላከው ኢ-ሜይል እንዳስታወቀው ፤ እንደገና በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ማይ ዓይኒ እና ዓዲ ሓሩሽ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ 10 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ይሰጥ የነበረው ርዳታ አሁን ላይ ተቋርጧል፡፡
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ነቨን ክሬቨንኮቪች፤ ጦርነቱ ከማገርሸቱ በፊት በኮሚሽኑ በኩል የሰብዓዊ እርዳታ ስራዎች ሲከናወን ቢቆይም አሁን ላይ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡
በትግራይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከመባባሱ በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ዩኤንኤችሲአር በጋራ በመሆን በመስከረም 13 እና 14 ቀን 2015 ዓ.ም በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ከ9 ሺህ 800 በላይ ስደተኞች የምግብ እርዳታ ማከፋፈላቸው ያስታወሱት ቃል አቀባዩ፤ አሁን ላይ የእርዳታው መቋረጥ ነገሮች ከባድ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡
በተለይም ወደ ትግራይ ሲደረግ የነበረው የተመድ የሰብአዊ አየር አገልግሎት በረራ በመቆሙ ምክንያት ለስደተኞች እርዳታ የሚሰጡ የዩኤንኤችሲአርን ጨምሮ ሌሎች ግብረሰናይ ሰራተኞች ወደ ትግራይ ክልል መግባት ባለመቻላቸውና የጥሬ ገንዘብ እቅረቦት ባለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በአማራ ክልል ዳባት አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ስለሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ ሲገልጹም፤ ከዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የሚደረገው ድጋፍ በቂ ነው የሚባል ባይሆንም፤ ስደተኞቹ እርዳታ የሚያገኙበት የተሻለ አድል እንዳለ አንስተዋል፡፡
“በአለምዋጭ የሚገኙ ስደተኞች መሰረታዊ የሰብአዊ ርዳታ (እንደ ሙቅ ምግብ፣ መጠለያ፣ ፍራሽ እና ብርድ ልብስ፣ ባልዲ እና ሳሙና) የመሳሰሉ ድጋፍ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የጤና አገልግሎትም የሚያገኙ ሲሆን ከባድና አስቸኳይ የህክምና ጉዳዮች ሲኖሩ በደባርቅ እና በጎንደር ወደሚገኙ ተቋማት እንዲላኩ ይደረጋል”ም ነው ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ስደተኞቹ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ የጤና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉና ከብሔራዊ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ጋር እንዲዋሃዱ ከባለስልጣናት ጋር መምከራችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።
በምግብ አቅርቦት ረገድ የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር 10 ሺህ ለሚሆኑ በአልመዋጭ ለሚገኙ ስደተኞች የሀምሌ እና ነሀሴን ወራት የምግብ ርዳታ ማሰራጨቱም አስታውቀዋል፡፡
ያም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተስተዋለው የነዳጅ ወጪ፣ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተከሰተው የሰብዓዊ ሀብቶች የመቀነስ ሁኔታ ለስደተኞች ሲደረጉ የነበሩትን የገንዘብ ድጎማዎችና የምግብ ራሽን 50 በመቶ ቀንሷል ብለዋል ቃል አቀባዩ ነቨን ክሬቨንኮቪች ።
“ብዙ ስደተኞች በቂ ምግብ ለማግኘት እየታገሉ ነው፣ ይህም የምግብ ዋስትናቸውን እና የተመጣጠነ ምግብን በእጅጉ ይጎዳል”ም ነው ያሉት፡፡
ከተጀመረ ሁለት አመት ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተለይም በትግራይ ክልል በነበሩት የኤርትራ ስደተኞች ላይ ያስከተለው ጉዳትና እንግልት ከባድ እንደሆነ የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ጦርነቱን ተከትሎ ወደ ከተማ የሚገቡ የስደተኞችን ቁጥር “በእጅጉ እንዲያሻቅብ” ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ ማማዱ ዲያን (ዶ/ር) በተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት ከተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ሸሽተው የመጡ በርካታ ስደተኞች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ በቅረቡ ለአል-ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ 30 ሺህ የነበረው የስደተኞች ቁጥር አሁን ላይ 80 ሺህ መድረሱንም የድርጅቱ ተወካይ ተናግረዋል።
ከየመጠለያ ጣቢያዎቹ ከሸሹት ስደተኞች መካከል በርካቶቹ ኤርትራውያን መሆናቸውም ነበር የገለጹት ተወካዩ፡፡