ህወሓት ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶብናል ሲል ከሷል
በሰሜን ኢትዮጵያው ጉዳይ ሰላም ለማምጣት ጥረት በማድረግ ላይ ያሉት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፤ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል መግባታቸው እናውቃለን ብለዋል፡፡
ማይክ ሐመር ይህን ያሉት የሰላም ድርድር ለማመቻቸት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ሲመለሱ በሰጡት መግለጫ ሲሆን የኤርትራን ድርጊት አውግዘዋል፡፡
“የኤርትራ ወታደሮችን በድንበር አከባቢ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ስንከታተል ቆይተናል …ይህ ድርጊት እናወግዘዋለን” ሲሉም ተናግረዋል ልዩ መልዕክተኛው፡፡
ሐመር ሁሉም የውጭ ተዋናዮች የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ማክበር እንዲሁም ግጭትን ከማባባስ መቆጠብ አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
ህወሓት በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ወታደሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደከፈተባቸው ገልጸዋል፡፡
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው ከተከዘ እስከ ኢሮብ ባሉ የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር የሚዋሰንባቸውን በርካታ አካባቢዎችን ላይ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
በጦርነቱ “የኢትዮጵያ መከላከያ እና የአማራ ኃይሎችና ሚሊሻ” ተሳትፈዋል ሲሉ የከሰሱት ቃል አቀበዩ፤ በማይ ኩህሊ፣ በዝባን ገደና፣ በአዲአውአላ፣ በራማ፣ በጾሮና እና በዛላምበሳ አካባቢዎች ከባድ ውጊያ እየተደረገ ነውም ብለዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኛውና የህወሓት ኃይሎች ይህን ይበሉ እንጅ፤ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ ትግራይ ገብተዋል በሚለው ጉዳይ ላይ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ መንግስታት በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም፡፡
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር ባለፈው ነሃሴ ድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማስቆም እና ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት አዲስ አበባ ሰንብተው ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡
ማይክ ሐመር ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በትናትናው እለት በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ዋነኛ እንቅፋት የሆነው “በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው አለመተማመን ነው” ብለዋል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ጦርነት በድርድር ለማብቃት አሜሪካንን ጨምሮ የአፍሪካ ህብረት ለወራት ሲያደርጉት የቆየውን የሽምግልና ጥረት ይህ ነው የሚባል ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሄ እንዳላመጣ በርካቶች የሚያነሱት ጉዳይ ነው፡፡
ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ቢሆንም ግን፤ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእከተኛ ማይክ ሐመር አሁንም የድርድር ተስፋ መኖሩ አመላክተዋል፡፡
ሁለቱም ወገኖች የጦርነት አማራጭን ትተው በጠረጴዛ ዙሪያ ለመቀመጥ የሚያስችል “ደፋር ውሳኔ እንደሚወስኑ ተስፋ አለን”ም ብለዋል ልዩ መልእክተኛው።
ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ድጋሚ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ጦርነቱን እንደ አዲስ በመጀመር መንግስት እና ህወሓት እርስ በእርስ ሲካሰሱ ይስተዋላል፡፡
ያም ሆኖ ሁለቱም አካላት የተደጀመረውን ሰላም ንግግር ጥረት እንዲቀጥል ዝግጁ መሆናቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር መግለጹ ይታወሳል፡፡
አፍሪካ ህብረት “ሰላም ሊያመጣ አይችልም” አስከማለት ደርሶ ነበረው ህወሓትም ቢሆን ፤በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁም ይታወሳል፡፡