የፌደራል መንግስት ህወሓት በወልቃይት፣ በዋግ እና በሱዳን በኩል ጥቃት መክፈቱን በትናንትናው እለት አስታውቋል
ህወሓት የኤርትራ ኃይሎች ጥቃት እንደከፈቱበት ገለጸ።
የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የኤርትራው መሪ "ኢሳያስ አፈወርቂ ሀይሎች" ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሆን በአራት አቅጣጫ በምእራብ በኩል በአድያቦ ጥቃት መክፈታቸውን በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል።
በተለያየ አቅጣጫ ጥቃት እንደተከፈተባቸው የገለጹት ቃል አቀባዩ ጥቃቱን እየመከቱት መሆኑን ገልጸዋል።
ኤርትራ በህወሓት ክስ ላይ እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
ህወሓት በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱን መንግስት ገለፀ
ከሁለት አመት በፊት የመጀመሪው ጦርነት ሲቀሰቀስ የኤርትራ መንግስት ኃይሎች የብሄራዊ ደህንነት ችግር ለመቀለበስ ሲሉ ወደ ትግራይ ክልል ገብተው እንደነበር የኤርትራ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።
ህወሓትና የኢትዮጵያ መንግስት ለወራት የቆየውን ተኩስ አቁም በመጣስ እንዳቸው ሌላኛቸውን በመክሰስ ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግስትም በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ህወሓት የወራራ አድማሱን በማስፋት በወልቃይት፣ በዋግ እና በሱዳን በኩል ወረራ ፈጽሟል ሲል አስታውቋል።
ለወራት ቆሞ የነበረው ጦርነት የተጀመረው በራያ በኩል ነው። በዚህ ግንባር የህወሓት ኃይሎች የቆቦ ከተማን ተቆጣጥረው በአካባቢው ጦርነት እያካሄዱ ነው።
የፌደራል መንግስት ህወሓት የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጥቃት መሰንዘሩን ገልጾ ከቆቦ ከተማ የከተማ ውጊያ ላለማድረግ ማፈግፈጉን መግለጹ ይታወሳል።
መንግስት ህወሓት በህዝብ ላይ ዳግመኛ በደል እንዳያደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በከማራ ክልል በሰቆጣ፣በወልዲያ፣ በደሴ እና በከምቦልቻ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰጋት የሰአት እለፊ ገደብ ተጥሏል።
ግጭቱን በድርድር ለመቋጨት ሁለቱም አካላት በተናጠል ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም ዳግም ወደ ግጭት ገብተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ሁቱንም አካላት በተደጋጋሚ ያገኘ ቢሆንም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት አላመጣም።
በመንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ለመደራደር ያለውን ዝግጁነት የገለጸ ሲሆን በህብረቱ ላይ ግን የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል።