የውድድሩ መስራች ከሆኑ ሶስት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከኬፕቨርዴ የምትጫወተው
33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ ካሜሩን ከቡርኪና ፋሶ በሚያደርጉት የምድብ አንድ ጨዋታ በያውንዴ ይጀመራል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ ካሜሩን የ2013 የውድድሩ የፍጻሜ ተፋላሚ የሆነችውን ቡርኪናፋሶን 60 ሺ መቀመጫዎች ባለትና በአዲሱ ኦሌምቤ ስታዲዬም ነው የምትገጥመው፡፡
በውድድሩ 20 ጊዜ የመሳተፍ ታሪክ ያላት ካሜሩን ከ50 ዓመታት በኋላም ነው ውድድሩን ያዘጋጀችው፡፡
ሌላኛው የምድብ አንድ ጨዋታ ምሽት 4፡00 ላይ በኢትዮጵያ እና ኬፕቨርዴ መካከል በዚሁ በኦሌምቤ ስታዲዬም ይካሄዳል፡፡
የውድድሩ መስራች ከሆኑ ሶስት ሃገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከኬፕቨርዴ የምትጫወተው፡፡
የውድድሩ የ1962 (እ.ኤ.አ) አሸናፊም ናት ኢትዮጵያ፡፡
ከ8 ዓመታት በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሱት ዋሊያዎቹ ለመፎካከር እና ያላቸውን ነገር ለማሳየት መዘጋጀታቸውን አልጣኝ ውበቱ አባተ ትናንት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
“ማንም ባይጠብቀንም ጥሩ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። በማጣርያው ላይ ቡድናችንን ተመልክታችሁታል። እንደከዚህ ቀደሙ አይነት ቡድን አይደለም ያለን” ሲሉም ነው አሰልጣኙ የተናገሩት፡፡
ስለ ተጋጣሚያቸው ስለ ኬፕ ቨርዴ ተጠይቀው “የመጀመርያ ጨዋታችን ነው። ስለዚህ ሁለቱም ቡድኖች እኩል እድል አላቸው። እነሱ ጠንካሮች ቢሆኑም እኛም የተሻለ ነገር ለማሳየት ዝግጁ ነን። ምድቡን በተመለከተ ቡድኖቹ ጠንካራ ናቸው፤ እናከብራቸዋለን። የተለየ ክብደት የምንሰጠው ቡድን ግን አይኖርም። ይህ እግር ኳስ ነው” ሲሉ መልሰዋል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊ እንደነበረች ያስታወሱት አሰልጣኙ በዚህ ውድድር ላይ የመጀመሪያ እቅዳቸው ከምድብ ማለፍ እንደሆነ ተናግረው ለመካፈል ብቻ ካሜሩን እንዳልተገኙ ገልጸዋል፡፡
“ለአህጉራችን እና ለዓለም ምን እንዳለን ለማሳየት ተዘጋጅተናል። በርካታ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች አሉን። ይህን ለእግርኳሱ ዓለም ማስተዋወቅ አለብን። በሌላ በኩል ሌሎቹ ቡድኖች ልምድ አላቸው። ግን የተለየ ነገር ለማሳየት እና ሰርፕራይዝ ቡድን ለመሆን ተዘጋጅተናል” በማለትም ነበር አሰልጣኝ ውበቱ ዓላማቸውን ያስቀመጡት፡፡