የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፓስፖርት ጠያቂዎች ያላግባብ 17 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ
ሰባት የመንግስት ተቋማት ከመንግስት ካዝና ያላግባብ ከ16 ሚሊዮን በላይ ብር ለግለሰቦች እንደከፈሉ ተገልጿል
የፌደራል መንግስት ተቋማት ከተፈቀደላቸው በጀት ውስጥ 19 ቢሊዮን ብሩ ሳይጠቀሙበት እንደቀሩ የፌደራል ኦዲተር አስታውቋል
የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ከፓስፖርት ጠያቂዎች ያላግባብ 17 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡ ተገለጸ።
የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2015 በጀት ዓመት የፌደራል መንግሥት ተቋማትን የበጀት ኦዲት ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላይ እንዳለው የኢምግሬሽን እና ዝግነት አገልግሎት ገንዘብ ለመሰብሰብ መመሪያ የማውጣት ስልጣን ሳይኖረው ከአገልግሎት ፈላጊዎች ያላግባብ ገንዘብ ሲሰበስብ እንደነበር ገልጿል።
ተቋሙ በተለይም የፓስፖርት ምዝገባ ቀን ቀጠሮ ያሳለፉ ግለሰቦችን በቅጣት ለማስተናገድ ከነሀሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም አካውንት እንደከፈተ ተገልጻል።
በተለይም ከመስከረም 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥር 2016 ዓ. ም ባሉት አምስት ወራት ውስጥ 17 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ገቢ አድርጓል ተብሏል።
ተቋሙ በዚህ መልክ ከሰበሰበው ገንዘብ ውስጥም ዘጠኝ ሚሊዮን ብሩን ለሰራተኞች ትርፍ ሰዓት እና ለበዓል ስጦታ እንደከፈለ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።
ተቋሙ ቪዲቸር ከተባለ የግል ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት ከሀገር ውጪ ያሉ ነዋሪዎች ለፓስፖርት አገልግሎት በበይነ መረብ ሲያመለክቱ ሰነዱን አጣርቶ ወደ ኢምግሬሽን የሚያስተላልፍ እንል ፓስፖርቱ ተዘጋጅቶ ሲያልቅ ከኢምግሬሽን ተቀብሎ ወደ ደንበኞች ተጨማሪ 100 ዶላር ክፍያ ያስከፍላል ተብላል።
ይሁንና ተቋሙ በምን መስፈርት እንደተመረጠ፣ የግዢ ሂደት እና ፓስፖርትን ለማሰራጨት ፈቃድ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ማቅረብ አልቻለም ተብሏል።
ከእያንዳንዱ በውጭ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አመልካቾች 100 ዶላር እንዲያስከፍል ፈቃድ የተሰጠው ቪዲቸር የተሰኘው ድርጅት በኢትዮጵያ ፈቃድ የሌለው፣ ከሚሰበስበው ገንዘብ ላይም ግብር የማይከፍል እንዲሁም የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የፓስፖርት አገልግሎቶችን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ እንዲሰጥ ሳይፈቀድለት ቪዲቸር ለተባለው የውጭ ሀገር ድርጅት አሳልፎ እንደሰጠ ዋና ኦዲተር አስታውቋል።
ይህ በዚህ እንዳለ የፌደራል ተቋማት በ2016 በጀት ዓመት ለስራዎቻቸው ማስፈጸሚያ ከተመደበላቸው በጀት ላይ 19 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ሳይጠቀሙበት ተገኝቷል ተብሏል።
የተመደበላቸውን በጀት ካልተጠቀሙ ተቋማት መካከል የገንዘብ ሚንስቴር፣ ጤና ሚንስቴር፣ ግብርና ሚንስቴር፣ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ወለጋ ዩንቨርስቲ ፣ ትምህርት ሚንስቴር እንዲሁም ውሀና ኢነርጂ ሚንስቴር ተጠቅሰዋል።
16 የመንግስት ተቋማት ስራ በለቀቁ እና ከስራ ለተሰናበቱ ሰራተኞች 485 ሺህ ብር እንደከፈሉ ዋና ኦዲተር በሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
እንዲሁም ሰባት የመንግስት ተቋማት 16 ሚሊዮን ብር አላግባብ ከመንግስት ካዝና ለግለሰቦች በቅጣት ስም እንደከፈሉም ተገልጿል።
ከመንግስት ካዝና በቅጣት መልክ ለግለሰቦች ክፍያ ከፈጸሙ ተቋማት መካከል በጉምሩክ ኮሚሽን የጅግጅጋ ቅርንጫፍ 10 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን 3 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የኢትዮጵያ ሚቲዮሮሎጂ ኢንስቲትዩት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ከፍለዋል።