ለአዲሱ ክልልም ም/ርእሰ መስተዳድርን ጨምሮ አፈ ጉባዔና ም/አፈ ጉባዔ ተመርጧል
የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን በጋራ 11ኛውን ክልል በይፋ መሰረቱ።
አምስቱ ዞኖች እነ አንድ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ ማድረጋቸው የሚታወስ ሲሆን ክልሉም በዛሬው እለት በይፋ ተመስርቷል።
አዲስ የተመሰረተውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት እንዲመሩት መመረጣቸው ተገልጿል።
የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመመረጥ በምክር ቤቱ ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።
ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ነበር።
ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ባለፉት ስርዓቶች የደረሰውን የአስተዳደር ስርዓት ስብራት የጎዳትን ሀገር መታደግ ከምንም በላይ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተደድሩ ለምክር ቤት አባላትና ለክልል መስራች አባላት ባደረጉት ንግግር፤ መንግስት “የህወሃት አሸባሪ ቡድን” ያደረሰውን እና እያደረሰ የሚገኘውን ጉዳት ለመከላከል የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።
ሕዝቡ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን ለማስጠበቅ ከምንም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆን እንደሚገባውም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በጉባኤው የክልሉ ምክር ቤት አባላት ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆኑን የክልሉን ህዝብ ለማገልገል ቃለ መሀላ የፈፀሙ ሲሆን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤም መርጠዋል።
በዚህ መሰረት አቶ ወንድሙ ኮርታ የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፤ ወይዘሮ ገነት መንገሻ ደግሞ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው በመመረጥ ቃለመሃላ ፈጽመዋል።
የክልሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ የጸደቀ ሲሆን÷ የዞን መዋቅሮች ደግሞ የራሳቸውን ቋንቋ እንደሚገለገሉ ተገልጿል።
የክልሉን ምስረታ በማስመልከትም የፌዴሬሽን ምክር ቤት “በድምፃችሁ ውሳኔያችሁን ማሳወቃችሁ የስልጡንነት መገለጫና የትክክለኛ ዲሞክራሲ ማሳያ ነው” ሲል የደስታ መግለጫ ልኳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ርዕሰ መስተዳድር ከሆኑ ወዲህ የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ክልልሎች ተመስረተዋል።
ረዘም ላሉ ዓመታት በክልል እንደራጅ የሚሉ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።