በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ይመሰረታል ተብሎ ለሚጠበቀው አዲስ ክልል ሕገ መንግስት እየተዘጋጀ ነው
በ2012 ዓ.ም የሲዳማ ክልልን በሕዝበ ውሳኔ ያዋለደችው ኢትዮጵያ ፣ ዘንድሮም ተጨማሪ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል እንደምታደርግ ይጠበቃል
ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሕዝበ ውሳኔ ክልል ከሆነ ከአንድ በላይ ዋና ከተሞች እንደሚኖሩት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ገልጿል
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ከሀገራዊ ምርጫው ጎን ለጎን በሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ሕገ መንግስት እየተዘጋጀለት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ምትኩ በድሩ (ኢ/ር) ፣ አዲስ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው ክልል የሰነድ ስራዎች እየተዘጁለት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን የሕዝበ ውሳኔው ውጤትና አጠቃላይ ዝግጅቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመራና የሚገለጽ ቢሆንም በሕዝበ ውሳኔው ውጤት ክልሉ የሚመሰረት ከሆነ በሚል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ነው ኢንጂነር ምትኩ የገለጹት፡፡ በዚህም መሰረት የክልል ስያሜ ፣ ሰንደቅ ዓላማ ፣ የሥራ ቋንቋና ሌሎችም ጉዳዮች የሚካተቱበት ሕገ መንግስት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተለያዩ ባለሙያዎች ተሰባስበው በሰነድ ዝግጅቶች ላይ እየሰሩ መሆኑንም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ምትኩ በድሩ (ኢ/ር) አንስተዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ እንዳሉት “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” በሕዝበ ውሳኔው አዲስ የፌዴሬሽኑ አካል ከሆነ በኋላ የጊዜ እጥረት እንዳይፈጠር በማሰብ ነው አሁን ላይ ሕገ መንግስት የማርቀቅ ስራው እየተከናወነ ያለው፡፡ የደቡብ ክልልም ይህ ጉዳይ እንዲሳካና ውጤታማ እንዲሆን እገዛ እያደረገ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ፕሮጄክት ማስፈጸሚያ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጁ እንደገለጹት ፣ አሁን ላይ ከሕገ መንግስትና መሰል ጉዳዮች ባለፈም ስለወደፊቱ የክልሉ ዋና ከተማም ውይይት እየተደረገና እየተሰራበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሰረት በሕዝበ ውሳኔው ደቡብ ምዕራብ ክልል ከተመሰረተ አንድ ዋና ከተማ ብቻ እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ክልል የሚዋቀር ከሆነ የመንግስት አገልግሎት የሚሰጥባቸው የተለያዩ ከተሞች እንደሚኖሩትና ይህም ለከተሞች ፍትሃዊ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አንስተዋል፡፡ ይህ ለሌሎችም አርአያ ሊሆን እንደሚችልም ነው ስራ አስኪያጁ ኢንጂነር ምትኩ የገለጹት፡፡
ሕገ መንግስትን ጨምሮ አሁን ላይ እየተዘጋጁ ያሉት የሰነድ ስራዎች ፣ ሕዝበ ውሳኔው ከተጠናቀቀ በኋላ የህዝብ ውይይት እንደሚደረግባቸውም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ሰኔ 14 ከሀገር አቀፍ ድምጽ መስጫ ዕለት ጋር በጋራ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ፣ በደቡብ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖችንና አንድ ልዩ ወረዳን በአዲስ ክልል ስር ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ የዞኖቹና የልዩ ወረዳው ነዋሪዎች በአንድ ክልል ለመደራጀት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም የተቋቋመው ይህ የፕሮጀክት ጽ/ቤት የአንድ ዓመት የቆይታ ጊዜ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት የከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ በአንድ ክልል ስር ለመደራጀት ያቀረቡት ጥያቄ ሰኔ 14 ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክትን ቀደም ብሎ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም የተያያዙ እጆች የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ የሚለውን እንደሚወክል መገለጹ ይታወሳል፡፡
የጎጆ ቤት ደግሞ የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ ቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ የሚለውን እንደሚወክልም ነው የተገለጸው፡፡
ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢህአዴግ በዘጠኝ ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ያዋቀራት ኢትዮጵያ አዳዲስ አወቃቀሮችን መለማመድ ጀምራለች፡፡ ሀገሪቱ በ2012 ዓ.ም የሲዳማ ክልልን በሕዝበ ውሳኔ ያዋለደች ሲሆን ፣ በዚህ ዓመትም ተጨማሪ ክልል የፌዴሬሽኑ አባል ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡