የፌዴሬሽን ምክር ቤት “ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ” 11ኛ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር ወሰነ
አዲሱ ክልል ከደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጋር የሥልጣን ርክክብ የሚያደርግ ይሆናል
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዳቸው ይታወሳል
ምክር ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክልልነት የህዝበ ውሳኔ ውጤትን መርምሮ አጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክልልነት የህዝበ ውሳኔ ውጤትን መርምሮ ያጸደቀው በዛሬው እለት ባካሄደው 6ኛ የፖርላማ ዘመን 1ኛ ዓመት የስራ ጊዜ አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የተከበሩ አቶ አገኙሁ ተሻገር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማሳወቁንና በአካል ቀርቦ ማብራራቱን በስብሰባው ለውይይት የሚሆን መነሻ ሀሳብ ማቅረባቸው ምክር ቤቱ ጥያቄውን እንዲያጸድቅ መጠየቃቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነትና የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ የአፈጉባኤውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ በጉዳዩ ላይ መክረዋል፡፡ምክር ቤቱ ከተቀመጡ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችና አግባብነት ባላቸው ሕጎች አንጻር መርምሮ ሕዝበ ውሳኔውን በሙሉ ድምጽ አጸድቀዋል፡፡
በዚህም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 11ኛ ክልል መሆኑን እውቅና አግንቷል፡፡
አዲሱ ክልል ከደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ጋር የሥልጣን ርክክብ ያደርጋል እንደሚያደርግም ይጠበቃል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ ራሳቸውን ችለው በክልልነት ለመደራጀት መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ አንድ የጋራ ክልል መመሥረቱን ደግፈው 1 ሚሊዮን 221 ሺህ 92 ድምፅ መስጠታቸው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማሳወቁንም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
በአንጻሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠልን ደግፈው 24 ሺህ 24 ድምጽ መስጠታቸው ይታወቃል።
ምክር ቤቱ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ወይም ራስን በራስ የማስተዳዳር ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊ እልባት መስጠት ነው።