የደቡብ ክልልና አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የስልጣን ርክክብ አደረጉ
በሁለቱ ክልሎች መካከል የሥልጣን፣ የሀብትና ዕዳ ክፍፍል የሚመራበት የውሳኔ ሀሳብ ጸድቋል
ክልሉ ሌሎች በክልል እንደራጅ የሚል ጥያቄ ላቀረቡ አካባቢዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እየሰራሁ ነው ብሏል
የደቡብ ክልል እና አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በዛሬው እለት የስልጣን ርክክብ ማድረገቸው ተገለፀ።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው ነው የስልጣን ርክክቡ የተካሄደው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ እርስቱ ይርዳ በዚሁ ወቅት፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምስረታ ሂደት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ሁነኛ ማሳያና ትልቅ ስኬት መሆን የሚችል ነው ብለዋል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስትን በመወከል ለአዲሱ ክልል ህዝቦች እንኳን ደስ አላችሁ መልካም ምኞታቸውንም ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዛሬው አስቸኳይ ጉባዔ፤ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች ክልል መንግሥት እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል የሚኖረውን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን በቀረበው የውሳኔ ሃሳብን አጽድቋል።
የፀደቀው የውሳኔ ሀሳብ የህዝበ ውሳኔውን ውጤት ተከትሎ ስለሚኖረው የሥልጣን ርክክብ፣ የሃብትና ዕዳ ክፍፍል እና ሌሎች መሠል አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመሩበትን መርህና አሠራር በግልፅ መደንገግ በማስፈለጉ እንደሆነ ተግልጿል።
በውሳኔ ሀሳቡ ላይም ሌሎች በክልል እንደራጅ የሚል ጥያቄ ላቀረቡ አካባቢዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ክልሉ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባሳለፍነው ቅዳሜ ባካሄደው ስበሰባው “ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ” 11ኛ ክልል ሆኖ እንዲዋቀር መወሰኑ ይታወሳል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ወረዳ ራሳቸውን ችለው በክልልነት ለመደራጀት መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ የድምፅ አሰጣጥ አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ አንድ የጋራ ክልል መመሥረቱን ደግፈው 1 ሚሊዮን 221 ሺህ 92 ድምፅ መስጠታቸው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በደብዳቤ ማሳወቁንም እንዲሁ የሚታወስ ነው።
በአንጻሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠልን ደግፈው 24 ሺህ 24 ድምጽ መስጠታቸው ይታወቃል።
ምክር ቤቱ ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት አንዱ የብሔር ብሔረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ወይም ራስን በራስ የማስተዳዳር ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊ እልባት መስጠት ነው።