ምላሹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተሰጠ ነው
ኢትዮጵያ ከሱዳን ለቀረበላት የ“በዝግ እንወያይ” ጥያቄ ምላሽ ሰጠች፡፡
በምላሿ “በግድቡ የድርድር ጉዳይ ላይ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ እንዲጠራ መጠየቁ ይበጃል” ብላለች፡፡
በሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጻፉት ባለው ደብዳቤ “በግድቡ የድርድር ጉዳይ ላይ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የህብረቱን ጉባኤ ለስብሰባ እንዲጠሩ መጠየቁ ሊበጅ እንደሚችል” ማስታወቃቸውን ገልጿል፡፡
ዛሬ ረፋድ ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሐምዶክ በጻፉት ደብዳቤ “የህብረቱ ጉባኤ ቢሮ ኃላፊነቱን ይውሰድ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በየትኛውም ዐይነት መድረክ የመገኘት ችግር የለባትም” ያሉት ቃል አቀባዩ “መፍትሔዎች ከህብረቱ ሳይታጡ እና ድርድሩ ሳይቋረጥ ለሌላ ድርድር መቀመጡ አስፈላጊ” እንዳይደለም ገልጸዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2015 በሱዳን ካርቱም የተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት መፍትሔ ሊገኝ የማይችል ከሆነ የተደራዳሪ ሃገራቱ መሪዎች ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንደሚችሉ ያስቀምጣል፡፡
ሱዳን ይህንኑ የተመለከተ ሃሳብ የተቀመጠበትን የስምምነቱን አንቀጽ 10 በመጥቀስ ነው የ“በዝግ እንወያይ” ጥሪ ለኢትዮጵያ እና ለግብጽ ያቀረበችው፡፡
ሱዳን እና ግብጽ በድርድሩ ሂደት ከአፍሪካ ህብረት ውጭ ሌሎች አካላት የአደራዳሪነት ሚና ይኑራቸው የሚል ሃሳብ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡