የሱዳኑ ጠ/ሚ ለግብጽ እና ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የ“በዝግ እንወያይ” ጥሪ አቀረቡ
የአሁኑ ጥሪ “የመጨረሻ አማራጮችን ለማጤን ያስችላል”ም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ያሉት
ሀምዶክ “10 ዓመታትን የፈጁ ድርድሮች ካለምንም ዉጤት መጠናቀቃቸው የሚያሳዝን ነው”ም ብለዋል
የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ለግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ ማድቦሊ እንዲሁም ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአስር ቀናት ውስጥ “በዝግ እንወያይ” የሚል ጥሪ አቀረቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከ10 ባልበለጡ ቀናት ውስጥ ተገናኝተን የድርድሩን ሂደቶች እንገምግም” ብለዋል፡፡
“በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መሰረት ወደፊት ለመራመድ በሚያስችሉን አማራጮች ላይ ተወያይተን እንስማማ፤ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነታችንንም እናድስ” ሲሉም ነው ሃምዶክ ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ጥሪው የቀረበው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረጉት ተደጋጋሚ የሶስትዮሽ ድርድሮች “ውጤታማ ሳይሆኑና ስምምነት ላይ ሳይደረስ ዓመታት በመቆጠራቸው” ነው፡፡
ሃምዶክ ለኢትዮጵያ እና ለግብጽ አቻዎቻቸው ጉዳዩን የተመለከተ መልዕክት ልከዋል፡፡
በመልዕክቱ “የግድቡ የግንባታ ስራ ከላቀ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ጊዜ የሚደረጉት የሶስትዮሽ ድርድሮች የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ያሉ ሲሆን “ቀጣይ ስራዎች ከመጀመራቸው በፊት ከስምምነት ላይ መድረሱ ‘አስቸኳይ እና እጅግ አስፈላጊ’” እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርድሩ ያለአንዳች የስምምነት ውጤት 10 ዓመታትን ማስቆጠሩ “የሚያስቆጭ ነው” ስለማለታቸውም ነው ከፅህፈት ቤታቸው የተገኘው መረጃ ያመለከተው፡፡
ምንም እንኳን “አሜሪካ እና ዓለም ባንክ በተሳተፉባቸው ድርድሮች መጠነኛ መሻሻሎች” የነበሩ ቢሆኑም አሁንም ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች አሉ ነውም ያሉት ሀምዶክ፡፡
በቅርቡ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ የተካሄደውን የሚኒስትሮች ስብሰባን ጨምሮ ከባለፈው ዓመት ወርሃ ሰኔ ጀምሮ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የተካሄዱ ድርድሮች ለስምምነት ለማብቃት አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ግብጽ በአፍሪካ ህብረት የሚመራ የአራትዮሽ ድርድር እንዲካሄድ ያቀረበችውን ሃሳብ ሃገራቸው ብትደግፍም ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ ምክንያት የኪንሻሳው ስብሰባ ሳይሳካ መቅረቱንም ነው ሃምዶክ የጠቀሱት፡፡
በድርድሩ ስምምነት ላይ ለመድረስ ካልተቻለ ጉዳዩ ለሃገራቱ መሪዎች እንዲተላለፍ በሚያዘው የመርሆዎች ስምምነቱ አንቀጽ 10 መሰረት የሶስቱ ሃገራት መሪዎች ዝግ የበይነ መረብ ስብሰባ እንዲያደርጉ ጥሪ ማድረጋቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ግድቡ “የአረብ ሃገራት የውሃ ደህንነት ስጋት” አድርገው ማቅረባቸው “ተቀባይነት” እንደሌለው ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአፍሪካ አምባሳደሮች ገለጻ በተደረገበት በትናንት ዕለት ማሳሰቧ የሚታወስ ነው፡፡