የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን መንግስት አስታወቀ
መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ አስቀምጧል
የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና በመከላከያ፣ በፌደራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት ይችላሉ ተብሏል
መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ የሚያስችል አንድ ጠንካራ የተማከለ ሠራዊት ለመገንባት አቅጣጫ ማስቀመጡን ገለፀ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ የየክልሉን ልዩኃይሎች ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ የሚያስችላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል።
በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት እንደ ምርጫቸውና እንደ ፍላጎታቸው በመከላከያ፣ በፌደራል ፖሊስ ወይም በክልል ፖሊስ አባልነት መካተት እንደሚችሉም በመግለጫው አመላክቷል።
“በዚህ ሐሳብ ላይም ከልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ጋር ከመግባባት ላይ ተደርሷል” ያለው መንግስት፤ “ቀደም ብሎም በሁሉም ክልል አመራሮች ጥናት ተደርጎበት፣ በተገኘው ውጤትም ያለምንም ልዩነት ውሳኔው ስምምነት ተደርሶበታል፤ ይህ ተግባር እንዲፈፀም መላ ህዝባችንም ሲጠይቅ ቆይቷል፤ ይሄንን ተከትሎም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተጀምሯል” ብሏል።
“የክልል ልዩ ኃይልን በተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የማካተት ውሳኔና የተግባር እንቅስቃሴ በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚከናወን ነው” ያለው መግለጫው፤ ይህ አካሄድ የኢኮኖሚ አቅምንን በማሰባሰብ የሠራዊታችንን የሥልጠና፣ የትጥቅና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ከፍተኛ ፋይዳ አለው። ይሄንን በመረዳትም በሁሉም ክልሎች ሂደቱ በመግባባትና በውይይት እየተከናወነ ይገኛል።
“ሆኖም በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ የልዩ ኃይል ክፍሎች ውስጥ፤ በአንድ በኩል የመልሶ ማደራጀት ሥራውንና ዓላማውን በአግባቡ ባለመረዳት፤ በሌላ በኩል የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ሆን ብለው በሚነዙት የሐሰት ወሬ በመጠለፍ ሂደቱን የሚያውኩ ተግባራት ታይተዋል” ብሏል መንግስት በመግለጫው።
“ከሚነዙት የሐሰት አጀንዳዎች መካከል፤ የመልሶ ማደራጀቱ መርሐ ግብር በአማራ ክልል ብቻ እየተካሄደ ነው፤ ሕወሐት ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት የክልሉ ልዩ ኃይል ትጥቅ ይፈታል የሚሉትናሌሎችም ይገኙበታል” ያለው መንግስት “እነዚህ አጀንዳዎች ሂደቱን ለማደናቀፍ በሚፈልጉ ኃይሎች እየተናፈሱ ይገኛሉ” ብሏል።
የክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ፕሮግራም በመላ ሀገሪቱ የሚተገበር ነው፤ ሥራውም በሁሉም ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኝ ነው፤ ሂደቱንም መንግሥት በጥናት፣ በዕቅድ እና በጥንቃቄ እየመራው ይገኛል፤ ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ተግባር በሚፈጸምበት ጊዜ።፣ በክልሎች አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሁሉም ቦታዎች ሥምሪት ወስዷል።
በሌላ በኩል ሕወሐት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሙሉ በሙሉ ትጥቅ እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የሕወሐት ትጥቅ የመፍታት ሂደት በተፈረመው ስምምነት መሠረት ያለማወላወል የሚፈጸም እንጂ ከሌላ ሀገራዊ ዕቅድ ጋር የሚቀናጅም የሚጣረስም አይደለም።
የሂደቱ ዋና ዓላማ የትኛውንም ልዩ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት አይደለም። ልዩ ኃይሉ ትጥቁን ይዞ እና የተሻለ ዐቅም ተፈጥሮለት በምርጫው መሠረት የክልል ፖሊስን፣ የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀል ማድረግ ነው።
በዚህ ሂደት መካተት የማይፈልግ ማንኛውም የልዩ ኃይል አባል ካለ መብቱ ተጠብቆ ወደ መደበኛ የሲቪል ሕይወት እንዲገባ መንግሥት አስፈላጊውን የማቋቋም ሥራዎች ይሠራል።
እንዲቋቋምም ድጋፍ እንደሚያደርግ ያስታውቃል። የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና የማደራጀቱ ሥራ መንግሥት ለዘላቂ የሀገር ጥቅምና ደኆንነት የወሰነው ውሳኔ በመሆኑ ኃላፊነቱንም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይወጣዋል። ስለዚህ በተለያዩ የጥፋት አጀንዳ አራጋቢዎች ከሚሠራጩ አሳሳች መረጃዎች በመራቅ መላው ሕዝብ እንዲሁም የክልል ልዩ ኃይል አመራሮችና አባላት ለመርሐ ግብሩ ስኬት እንዲረባረቡ መንግሥት ያሳስባል።