የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፤ መንግሥት ለሕዝብ ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠየቀ
ገዢው ፓርቲ አባል የሆነበት ምክር ቤቱ መንግስት ግዴታውን ባለመወጣቱ ችግሮች መባባሳቸውንም ገልጿል
ም/ቤቱ፤ መንግስት “የደህንነት ስጋት አለብን” ላሉ ዜጎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ነበረበት ብሏል
ገዢው ፓርቲ አባል የሆነበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር፤ የሀገርን ሠላምና የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ይህንን አለማድረጉን ገለጸ።
የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊና የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ም/ፕሬዝዳንት ራሄል ባፌ (ዶ/ር) ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሁን ያለውን ግድያ መቆም ያልቻለው መንግስት “ቁርጠኛና ግልጽ ስላልሆነ ነው” ብለዋል።
ከሰሞኑ ለሁለት ቀናት ስብሰባ ያደረገው የብልጽግና ማዕከላዊ ኮሚቴ የሕግ ማስከበር ስራ እየሰራ መሆኑን ቢገልጽም ዶ/ር ራሄል ግን መንግስት ቁርጠኛ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የመንግስት ተግባር እርምጃ መውሰድ ሳይሆን ቀድሞ መከላከልና ዜጎችን መጠበቅ እንደሆነም ዋና ጸሐፊዋ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
ዜጎች ሀገራቸው እንደሆነ በማመን ቀደም ብለው በመንግስት አነሳሽነት በሰፈራ ወደሌላ ቦታ ቢሄዱም አሁን ግን ከፍተኛ ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነም ነው የገለጹት።
ዶ/ር ራሄል መንግስት የሰፈራ ጣቢያዎችን አስቀድሞ ሊጠብቅ እና ሊከላከል ይገባ እንደነበር ገልፀዋል።
የትኛውም የኢትዮጵያ መሬት የዜጎች እንጅ የብሔር መሆን እንደሌለበትም የገለጹት ዋና ጸሀፊዋ፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ መሬትን ለብሔር የሰጠ መሆኑ አደገኛ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።
የማንኛውም መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር፤ የሀገሩን ሠላምና የዜጎቹን ደኅንነት መጠበቅ እንደሆነ ቢታወቅም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ግዴታውን በተሟላ መልኩ ሊወጣ አልቻለም” ሲሉም ነው የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊና የኢሶዴፓ ምክትል ፕሬዝዳንት የገለጹት።
በምዕራብ ወለጋ ፣ በጋምቤላ ፣ በቤኒሻንጉል ፣ በደቡብ እና በሌሎችም የሀገሪቱ ክልሎች በግፍ ለተገደሉ ንፁሃን ዜጎች መታሰቢያ የሚሆን የብሔራዊ ሐዘን ቀን እንዲታወጅም የሕዝብ ተወካዮችን ምክር ቤትን መጠየቁ ይታወሳል።
የጋራ ምክር ቤቱ፤ መንግሥት በፍጹም ቅንነትና ቁርጠኛነት ለሕዝብ ደህንነትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለንጹሐን ሞትና ሲቃ ወቅታዊ ፍትሕ በመስጠት ኃላፊነቱን በታማኝነት እንዲወጣ ጠይቋል።