መንግሥት በህወሀት አመራሮች ላይ የመሰረተውን ክስ አቋረጠ
ክስ የተቋረጠው የፌደራብ መንግሥት እና ህወሀት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ነው
ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ተመስርተው የነበሩ ክሶች በሽግግር ፍትህ ስርዓት ይታያሉ ተብሏል
መንግሥት በህወሀት አመራሮች ላይ የመሰረተውን ክስ አቋረጠ።
አቃቤ ህግ የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑትን ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልን ጨምሮ በሌሎች በ62 ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን መስርቶ እንደነበረ ይታወሳል።
ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች የህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ(ህወሓት)አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት፤ ውሳኔ በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የህውሀት መዓከላዊ ኮሚቴ አባላትና የክልል መንግስቱ ካቢኔ አባላት መሆናቸውን አቃቤ ህግ ግልጿል።
የፍትህ ሚንስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫው በወንጀል ተጠርጥረው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩ የህወሓት ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮች ክስ መቋረጡን አስታውቋል
ሚኒስቴሩ በመግለጫው፤ በፌዴራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ህወሓት) መሃከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት ከግጭቱ ጋር ተያያዥ የሆኑ ወንጀሎች ተጠያቂነት በተመለከተ ያለውን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ሊታዩ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብላል።
ክሱ የተቋረጠላቸው ተከሳሾች ጉዳያቸዉ በቀጣይ በሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ እንደሚታይም ተገልጿል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ቀርቦ በክርክር ሂደት ላይ ይገኙ የነበሩ የወንጀል ክሶች በአዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6 (3) (ሠ) መሰረት መነሳታቸውን ሚንስቴሩ ገልጻል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህወሀት ላይ አጽድቆት የነበረውን የሽብርተነት መዝገብ ባሳለፍነው ሳምንት ማንሳቱ ይታወሳል።