በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ በተፈጠረ ችግር የ3 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለፀ
በዩኒቨርስቲው ፈተናውን ያልወሰዱ 16 ሺህ ተማሪዎች ዳግም እንደሚፈተኑ ትምህርት ሚንስቴር አስታወቀ
ሚንስቴሩ "ፈተናው ከስርቆትና ከኩረጃ ነጻ ሆኖ ተጠናቋል" አለ
የትምህርት ሚንስቴር የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና "የጎላ ችግር" ሳያጋጥም ተጠናቋል አለ።
የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ ሚንስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በሰጡት መግለጫ፤ ፈተናው ከስርቆትና ኩረጃ ነጻ ሆኖ ተጠናቋል ብለዋል።
በአጠቃላይ 841 ሽህ ገደማ ተማሪዎች በ2 ሽህ 785 የፈተና ጣቢያዎች ፈተናውን መውሰዳቸው ተነግሯል።
ፈተናውን ይሰጥ በነበረው ጎንደር ዩኒቨርስቲ በተፈጠረ ችግር ሦሶት ሰዎች መገደላቸውን ሚንስቴሩ አስታውቋል።
አንድ የፈተና አስፈጻሚ እና ሁለት የፌደራል ፖሊሶች በ"ኢ-መደበኛ ኃይሎች" መገደላቸው ተነግሯል።
በዩኒቨርስቲው ሦስት ካምፓሶች አጋጠመ በተባለው ችግር 16 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን አለመፈተናቸውን ሚንስቴሩ አክሎ ተናግሯል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በቀጣይ በሚመቻች መርሀ ግብር ተማሪዎቹ ፈተናውን እንደሚፈተኑ አስታውቀዋል።
ሚንስትሩ የትራፊክ አደጋ፣ ህመም፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም፣ ያልተፈቀዱ ቁሳቁሶችን ወደ ፈተና ጣቢያ ይዞ ለመግባት መሞከር እና የስነ-ምግባር ችግሮች ማጋጠማቸዉን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገር ግን በፈተናው ሂደት "የጎላ ችግር" አለማጋጠሙንም ጠቁመዋል። የዘንድሮ ሀገር አቀፍ ፈተና ከሀምሌ 19 እስከ ሀምሌ 28፤ 2015 ዓ.ም በሁለት ዙር ተሰጥቷል።
ከ30 ሽህ በላይ የፈተና አስፈጻሚዎች ፈተናውን ማሳለጣቸው ተነግሯል።
ሚንስቴሩ የ2015 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና "በስኬት" እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርቧል።