ብሔራዊ ባንክ ለአምስት የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የስራ ፈቃድ ሰጠ
ቢሮዎቹ ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት ተሳትፎ ይኖራቸዋል ተብሏል
መንግስት ባሳለፍነው አመት ይፋ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን ማድረጉ ይታወሳል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለአምስት ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የስራ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ባወጣው መመሪያ መሰረት ለምንዛሪ ቢሮዎቹ ፈቃድ መስጡን ገልጿል።
አሁን በሥራ ላይ ካሉት ባንኮች ጋር ከተያያዙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ከባንክ ጋር ዝምድና የሌላቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መመሪያ (NBE Foreign Exchange Directive No. FXD/01/2024) እንዳወጣ አስታውሷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋትና ለማዳበር የሚረዳ ሚና እንደሚኖራቸው ነው ባወጣው መግለጫ ያመላከተው፡፡
ቢሮዎች በዋናነት የሚያካሂዱት የውጭ ምንዛሪ ሽያጭም ሆነ ግዥ ወዲያውኑ እጅ በእጅ የሚፈጸም ግብይት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ፈቃድ ያገኙት ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት ይችላሉ፡፡
ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉም ነው ብሄራዊ ባንክ የገለጸው።
ባንኩ ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸው ተረጋግጦ በመመሪያው መሠረት እንዲንቀሳቀሱ የሥራ ፈቃድ የሰጣቸው የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች፦
1. ዱግዳ ፊደሊቲ ኢንቨስትመንት ፒኤልሲ
2. ኢትዮ ኢንዲፔንደንት ፎሬን ኤክስቼንጅ ቢሮ
3. ግሎባል ኢንዲፔንደንት ፎሬን ኤክስቼንጅ ቢሮ
4. ሮበስት ኢንዲፔንደንት ፎሬን ኤክስቼንጅ ቢሮ
5. ዮጋ ፎሬክስ ቢሮ ናቸው።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ የአሠራር፤ የደህንነት፣ የሪፖርት አደራረግና የመዝገብ አያያዝ መስፈርቶችን በአግባቡ ተግባራዊ ስለማድረጋቸው ባንኩ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል አደርጋለሁ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት በ2016 ሀምሌ ወር ላይ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሬ በገበያ እንዲወሰን መፍቀዱ ይታወሳል፡፡
በዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ከተባለው አዲስ አሰራር መካከል ለግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ መስጠት የሚለው ይገኝበታል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ዛሬ ጠዋት ባደረገው ስብሰባ በቅርብ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አፈፃፀም መገምገሙን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በዚህም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ፥ "ፖሊሲው ተፈፃሚ በሆነባቸው ሁለት ወራት የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ከባቢን መመልከት ችለናል" ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡