ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ዶላር ለመሸጥ ያወጣውን ልዩ ጨረታ ውጤት ይፋ አደረገ
በጨረታው የተሳተፉ 27 ባንኮች ያቀረቡት አማካይ የዶላር መግዣ ዋጋ 107.9 ብር መሆኑን ነው ብሔራዊ ባንክ የገለጸው
የዛሬው ልዩ ጨረታ በነገው እለት በሚወጣው እለታዊ የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች ዶላር ለመሸጥ ያወጣው ልዩ ጨረታ ውጤትን ይፋ አድርጓል።
በዛሬው እለት በተካሄደው ልዩ ጨረታ 27 ባንኮች የሚፈልጉትን የዶላር መጠን እና የሚገዙበትን ዋጋ አስገብተው ተጫርተዋል።
ባንኮቹ ለአንድ ዶላር ያቀረቡት አማካይ የመግዣ ዋጋ 107.9 ብር መሆኑን ባንኩ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ጨረታው በነገው እለት ባንኮች በሚያወጡት እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚያደርግ ይጠበቃል ብሏል ብሔራዊ ባንክ።
የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ የዶላር ሽያጭ ጨረታው ውጤትን ሲገልጹ፥ ባለፉት ቀናት በባንኮች እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም የውጭ ምንዛሬ መረጋጋትን ያመጣል ያሉት አቶ ማሞ፥ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ሁሉንም የውጭ ምንዛሬ እንቅስቃሴ ወደ ባንክ ስርአት የማስገባት ትልም መያዙን አብራርተዋል።
በዚህም የውጭ ምንዛሬ የሚሹ አስመጪዎችና ሌሎች ኩባንያዎች ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረው ችግር እንደሚፈታ ነው ያነሱት።
ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያው እንዲመራ ካደረገች በኋላ ባንኮች አስመጪ ደንበኞቻቸው ለሚያቀርቡት የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ እየሰጡት ያለው ምላሽ አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደችው ልዩ የውጭ ምንዛሬ ጨረታ ማዕከላዊ ባንኮች ከንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሚገዙበት ወይም የሚሸጡበት አሰራር ነው።
ጨረታው በውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ የሚታይ ጫናን ለማቃለልና በግልና መንግስት መካካል ያለውን የምንዛሬ ልዩነት ለማጥበብ እንደሚረዳ ይታመናል።
ብሔራዊ ባንክ በገበያ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በቀጣይ ሳምንታትም ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ በጨረታ ሊያከናውን እንደሚችል በትናንትናው እለት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ተግባራዊ ካደረገች ዛሬ 10ኛ ቀኗን የያዘች ሲሆን፥ የዶላር የምንዛሬ ዋጋ ከ40 ብር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።